በጊፋታ በዓል ላይ የታየው ሕብረ ብሔራዊ የአንድነት ዕሴት የህዝቦችን ዘመናት የዘለለ ትስስር ማሳያ ነው....አቶ ርስቱ ይርዳው

133
ኢዜአ (ሶዶ) መስከረም 19 ቀን 2012 ዓ.ም---በወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ ጊፋታ በዓል ላይ የታየው ሕብረ ብሔራዊ የአንድነት ዕሴት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዘመናት የዘለለ ትስስር እንዳላቸው ማሳያ በመሆኑ ሊጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ፡፡ “ የጊፋታ በዓል ለኢትዮጵያ አንድነትና ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል ከሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተወካዮች በተገኙበት በተለያዩ ባህላዊ ስርዓቶች በሶዶ ከተማ በድምቀት ተከብሯል፡፡ በበዓሉ የተገኙት የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው የወላይታ ብሔር የመተሳሰብ፣ የአንድነትና የመከባበር ባህሉንና ዕሴቱን ጠብቆ ያቆየ ስለመሆኑ የጊፋታ በዓል አንድ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል። በአገሪቱ የተጀመሩ የለውጥ ሂደቶችን ተከትሎ የገጠሙ ፈተናዎች ለውጡን እንዳያጨናግፉ የብሔሩ ተወላጆች በተባበረ ክንድ፣ በውይይት፣ በትዕግስትና በጽናት ለማለፍ ላሳዩት ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ የጊፋታ በዓል የዘመን መለወጫ፣ የመንፈስ ማደሻ፣ የይቅርታና ዕርቅ በዓል ከመሆንም በላይ ልጃገረዶችና ጎረምሳዎች የፍቅር አጋራቸውን የሚመርጡበት መሆኑንም ተናግረዋል። በበዓሉ ላይ የታየው ሕብረ ብሔራዊ የአንድነት ዕሴት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዘመናት የዘለለ ትስስር እንዳላቸው ስለሚያሳይ ሊጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል። “በዓሉ የዴሞክራሲ ስርዓት፣ የመመካከርና የምክንያታዊነት ተምሳሌት በመሆኑም ማጎልበት ይገባል” ሲሉ ነው የገለጹት። አዲሱን ዓመት መቀበል የሚገባው በክልሉ የሚገኙ ምሁራን፣ ወጣቶችና ነዋሪዎች የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ በማጠናከር፣ ሠላምን በመጠበቅና በመደመር ዕሳቤ ሊሆን እንደሚገባም አቶ ርስቱ ተናግረዋል። አገሪቱን ወደብልጽግና ለማምጣት የተጀመረውን አገራዊ እንቅስቃሴ እውን ለማድረግ ቃል በመግባት ጭምር መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኩምቤ ነገን ብሩህ ለማድረግ የብሔሩ ቱባ ባህልን ማጎልበትና የጊፋታን በዓል በጋራ ለማክበር የተጀመረው ጥረት መጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል። “በምንም ሊበጠስ የማይችል ዘመን ዘለል ትስስራችንና ውበታችንን ለማጠናከርና ኢትዮያዊነትን ለማጎልበት ሲባል በዓሉ በጋራ እንዲከበር ተደርጓል” ብለዋል። የጊፋታ በዓል በህዝቦች መካከል የአንድነት፣ የአብሮነትና የመቻቻል ባህል እንዲጎለብት በማድረግ በኩል ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ በዓሉን በጋራ ማክበር በቀጣይም ሊጠናከር እንደሚገባ ነው የገለጹት። የብሔሩ ተወላጆች ኢትዮጵያዊ አንድነትንና ከሌሎች ህዝቦች ጋር ተሳስቦ አብሮ የመኖር ባህላቸውን በማጠናከር ለአገሪቱ ብልጽግና ተግተው እንዲሰሩም አቶ ዳገቶ ጥሪ አቅርበዋል። በበዓሉ ላይ ባዩት የህዝቦች አንድነት መደነቃቸውን የገለጹት የኢህአዴግ እና የህወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልናየትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ተወካይ አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፣ የወላይታ ህዝብ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር አንድነቱን ጠብቆ በሰላም በመኖር የሚታወቅ መሆኑን ተናግረዋል። የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ ጊፋታ በዓልን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የዞኑ አስተዳደር የጀመራቸውን ተግባራት ክልላቸው እንደሚደግፍም አመልክተዋል። “በራስ ማንነትና በኢትዮጵያዊ ማንነት መካከል ግጭት ሊኖር እንደማይችል የጊፋታ በዓል አሳይቶናል” ያሉት አቶ ጌታቸው ሰላምን ለማጠናከርና የኢትዮጵያን አንድነት ቀጣይ ለማድረግ አንዱ ከሌላው ጋር በመደጋገፍና ትስስሩን በማጠናከር ሊኖር እንደሚገባ አመልክተዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር የፕሬስ ሴክረተሪያት ጽህፈት ቤት ኃላፊና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ተወካይ አቶ ንጉሱ ጥላሁን “የመስቀልና የጊፋታ በዓላት መገጣጠም መልክ፣ ቋንቋና ባህላችን ቢለያይም ኢትዮጵያን ታላቅ ማድረግ የሚያስችል የጋራ አንድነትና ልምድ እንዳለን ያሳያል” ብለዋል፡፡ የአማራና የወላይታ ህዝቦች ለረጅም ዘመናት የተሳሰረ ታሪክ ባለቤት መሆናቸውንም አቶ ንጉሱ  ተናግረዋል። እንደ አቶ ንጉሱ ገለጻ ትዕግስት፣ ሥራ ወዳድነትና አብሮ የመኖር ባህልና ልምዶችን ከማጠናከር ባለፈ በታሪክ ተከስተው ያለፉ ቁርሾና ቂሞችን በመተው በይቅርታ መታደስ ይገባል። “ከጊፋታ በተማርነው ልክ ሠላማችንን በማጠናከር አዲስ ምዕራፍ ለመክፈትና የኢትዮጵያን ብልጽግና ዕውን ለማድረግ እንረባረብ” ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡ በበዓሉ ላይ የጎንደር ቤተመንግስትና የአክሱም ኃውልት እንዲሁም ጌዴኦ የሚታወቁበትን ጥምር እርሻ የሚያሳዩ ስዕሎች ለወላይታ ዞን አስተዳደር በስጦታ ተበርክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም