በበርሊን የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወንዶችና በሴቶች አሸነፉ

115
መስከረም 18/2012 በበርሊን ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወንዶች ከአንድ እስከ ሶስት በሴቶች አንደኛና ሁለተኛ በመውጣት ውድድራቸውን አጠናቀዋል። ዛሬ በጀርመን በተካሄደው የበርሊን ማራቶን ውድድር ቀነኒሳ በቀለ ጥሩ ሰዓት በማስመዝገብ አሸናፊ ሆኗል፡፡ ቀነኒሳ ውድድሩን የፈፀመው ሁለት ሰዓት ከአንድ ደቂቃ ከ41 ሰከንድ በመግባት ነው፡፡ ቀነኒሳ የዓለም ሪከርድ ለመስበር ሁለት ሰከንድ ብቻ ነበር የቀረው፡፡ በኦሎምፒክና በዓለም አትሌቲክስ ውድድር በ5 ሺህ እና በ10 ሺህ ኪሎ ሜትሮች አሸናፊ የሆነው ቀነኒሳ አሁን ያስመዘገበው ውጤት ሁለተኛው ፈጣን ሰዓቱ መሆኑን  የዓለማቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በድረገጹ አስነብቧል፡፡ ሌላው ኢትዮጵያዊ ብርሃኑ ለገሰ ከቀነኒሳ በአንድ ደቂቃ በሰባት ሰከንድ ዘግይቶ በመግባት ሁለተኛ ወጥቷል፡፡ ሲሳይ ለማ ሁለት ሰዓት ከ03 ደቂቃ ከ36 ሰከንድ በመግባት ሶስተኛ መወጣቱን ድረገጹ አስነብቧል፡፡ አትሌት ቀነኒሳ ከውድድሩ በኋላ በሰጠው አስተያየት ቀደም ሲል ተይዞ የነበረውን የማራቶን ሪከርድ ማሻሻል ባለመቻሉ ማዘኑን ቢገልጽም "ተስፋ አልቆርጥም ሪከርዱን አንድ ቀን በእጄ አስገባለሁ" በማለት ቁጭቱን ተናግሯል። ቀነኒሳ በቀጣይ ለሌላ ውድድር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ብርታት እንደሚሆነው ገልጿል። በሴቶችም ኢትዮጵያዊቷ አሸቴ በከሬ በ2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ከ14 ሰኮንድ አንደኛ ስትወጣ ማሬ ዲባባ በ7 ሰኮንድ በመዘግየት ሁለተኛ ወጥታለች። ኬንያዊቷ ሳሪ ቺፕዬጎ ደግሞ በ2 ሰዓት ከ21 ደቂቃ ከ06 ሰኮንድ ሶስተኛ ወጥታለች።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም