ለወጣቱ አዎንታዊ አስተሳሰብ ወላጆችና መምህራን ኃላፊነት አለባቸው-ምሁራን

175
አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 18/2012 ወጣቱ አዎንታዊ አስተሳሰብን እንዲላበስ ወላጆችና መምህራን በጎነትን በተግባር ማስተማር እንደሚገባቸው ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ምሁራን ገለፁ። ሀገራት ያደጉት በተሻለ አስተሳሰብ በመሆኑ የስነ-አዕምሮ ባለሙያዎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስለ አዎንታዊ አስተሳሰብ በመንገር ወጣቱም መልካም አስተሳሰቦችን በመገንባት ለሀገር ብልፅግና አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ነው ምሁራኑ የተናገሩት። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ስነልቦና ባለሙያው ዶክተር ያሲን መሐመድ እንዳሉት ሰብዕናን ለመገንባት አስተሳሰብ፣ ስሜትና ባህሪ ላይ መስራት ይገባል። እነዚህ "ሶስት ነገሮች የተያያዙ ናቸው" ያሉት ዶክተር ያሲን፤ በተለይ የአንድ ሰው አስተሳሰብ ለስሜቱና ባህሪው ወሳኝ ነው ብለዋል። አንድ ሰው ጥሩ ነው ብለን ካሰብን ያንን ሰው እንወደዋለን፤ ይህም አስተሳሰብና ስሜት የተያያዙ መሆናቸውን ማሳያ በመሆኑ ነው ብለዋል። አዎንታዊ አስተሳሰብ ስናስተምር መልካም ሰብዕናን መገንባት እንችላለንም ብለዋል። አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ አስተሳሰብ በሂደት የሚመጡ በመሆናቸው አስተሳሰብን መቀየር ጊዜ የሚወስድ እንደሆነም አስረድተዋል። አዎንታዊ አስተሳሰብ ጊዜ ተሰጥቶ ሊሰራበት የሚገባ በመሆኑ መልካም አስተሳሰብ ያላቸው አርአያዎችን በማየት የሚገነባና ማሳመንን የሚጠይቅ መሆኑንም ገልፀዋል። አዎንታዊ አስተሳሰብ በመደጋገምና ከታች ጀምሮ የሚመጣ በመሆኑም ትምህርት ቤትና ቤተሰብ ስለበጎነትና ጥሩ መሆን ማስተማር እንዳለባቸውም ተናግረዋል። የአንድ ሰው ሰብዕና በራሱና በኀብረተሰቡ እንዲሁም በተቋማት ጭምር የሚገነባ በመሆኑም "በአንድ ሰው ሰብዕና ውስጥ በርካታ ወገኖች አሉ" ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ዶክተር ጠና ደዎ ናቸው። መልካም ሰብዕና ለመገንባት "በመልካም አስተሳሰቦችና በእምነት መታነፅ ያስፈልጋል" ያሉት ዶክተር ጠና፤ ይህም የሚመጣው በጊዜ ሂደት ነው ይላሉ። ወጣቱ በአሁኑና በሚቀጥለው ትውልድ ውስጥ የሚኖር የሁለት ትውልድ ሰው በመሆኑም "ድርብ ኃላፊነት እንዳለበትም" አስረድተዋል። ወጣቱ ዛሬ ባለው ትውልድ ውስጥ ካለው ኃላፊነት በተጨማሪ ነገ የተሻለ ህይወት እንዲኖር ዛሬ የሚከውናቸው ተግባራቱና የሚያንፀው ባህሪያቱ ወሳኝ መሰረት ናቸውም ብለዋል። ወጣቱ አዎንታዊ አስተሳሰቦችና መልካም እይታዎችን እንዲላበስ ወላጆች፣ ትምህርት ቤት፣ ተቋማትና ሁሉም ሚናው የጎላ መሆኑንም አውስተዋል። በአሁኑ ወቅት "ለዘብተኝነትና ምንአገባኝ የሚል ሰው" እየተበራከተ መሆኑን ገልፀው፤ ወጣቱ የሁላችንም ነው በሚል እሳቤ ኀብረተሰቡ ወጣቱን በመንከባከብ ወደአዎንታዊ አስተሳሰብ ለመመለስ ሚናውን መወጣት አለበትም ብለዋል። ምሁራኑ ወጣቱ ራሱን ከኢንተርኔት ሱሰኝነት ባርነት ነፃ በማውጣት በበጎ ተግባራት ላይ እንዲያተኩርም አሳስበዋል። ከዚህ በተጨማሪም አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ አስተሳሰብ በራስ የሚመጣ በመሆኑ ወጣቱ መልካም አስተሳሰብ ለማዳበር እንዲተጋም መክረዋል ምሁራኑ። ዶክተር ያሲን መሀመድ እንዳሉት  “ሀገር የሚገነባው በጭንቅላት ነው፤ ብዙ ሀገሮች ያደጉትም በአስተሳሰብ ነው፤ የስነ አዕምሮ ባለሙያዎች በተለይ ባገኙት አጋጣሚ ስለ አዎንታዊ አስተሳሰብ መንገር ይገባቸዋል፣በጎ አስተሳሰብም ሆነ ቀናያልሆነ አስተሳሰብ በራሳችን ነው የሚመጣው እያንዳንዱ ወጣት በጎ አስተሳሰብ እንዲያዳብር እመክራለሁ።” “ወጣቱ ድርብ ኃላፊነት ነው ያለበት፤ ዛሬ የሚጠበቅበት ነገር አለ፤ ነገ ደግሞ ከዛሬ የበለጠ የሚጠበቅበት ነገር አለ፤ ይሄን ድርብ ኃላፊነቱን ለመወጣት ምን ጊዜም ቢሆን መጣር አለበት፤ አልባሌ በሆኑ ጉዳዮች መጠመድ የለበትም፤ ከሱስ ራሱን ማራቅ አለበት። ሱስ ስንል ዕፅዋትን ብቻ መውሰድ አይደለም ለምሳሌ ኢንተርኔት ራሱ በአሁኑ ሰዓት ሱስ ሆኗል፤ ሱስ ባርነት ነው ራስን መቆጣጠር ፣መግዛትና መምራት አይቻልም ፣ሱስ ካለባቸው ከእንዲህ አይነቱ ነገሮች ራሳቸውን ነፃ ማድረግ አለባቸው። እጃቸውን መስጠት የለባቸው"ያሉት ደግሞ ዶክተር ጠና ደዎ ናቸው፡፡ ወላጆችና ማህበረሰቡ ከሚያደርገው የትውልድ ቀረጻ በተጨማሪ የስነ አዕምሮ ባለሙያዎችም ባገኙት አጋጣሚዎች ሁሉ በተለይም በትምህርት ቤቶች ስለ አዎንታዊ አስተሳሰብ እንዲያስተምሩ ምሁራኑ ጠይቀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም