የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ወይዘሮ ኑራ እንድሪስ አረፉ

120
መስከረም 17/2012 በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህዝብ ተወካይ የነበሩት ወይዘሮ ኑራ እንድሪስ አረፉ፡፡ የህይወት ታሪካቸው እንደሚያስረዳው ወይዘሮ ኑራ እድሪስ በ1955 ዓ.ም. ከአባታቸው አቶ እድሪስ በላ እና ከእናታቸው ከፋጡማ አሊ  በአሶሳ ከተማ ነው የተወለዱት፡፡ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምርታቸውን በአሶሳ ከተማ የተከታሉ ሲሆን በማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪአቸውን አግኝተዋል፡፡ በወጣትነታቸው በቀድሞው የበርታ ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ (በህነን) አማካኝነት የክልሉ ህዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ነጻነት እንዲጎናጸፍ ታግለዋል፡፡ ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስም ከወረዳ እስከ ክልል ሴቶች ጉዳይ እና ሌሎችም ተቋማት በተመደቡበት ወቅት የተሠጣቸውን ሃላፊነት በትጋት ሲወጡ ቆይተዋል። በተለይም ወላጅ አልባ ህጻናትን በመደገፍ ያደረጉት አስተዋጽኦ በአርአያነት እንደሚጠቀስ የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ ከ1992 ዓ.ም. ጀምሮ የአሶሳ ወረዳ ህዝብን በመወከል ለሁለት ተከታታይ የምርጫ ዘመናት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆን የህዝባቸውን ድምጽ ሲያሰሙ ቆይተዋል። ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው ዛሬ በተወለዱ በ57 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ የቀብር ስነ-ስርዓታቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰንን  ጨምሮ ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸውና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በዛሬው ዕለት በአሶሳ ከተማ በሙስሊም መካነ መቃብር ተፈጽሟል፡፡ ወይዘሮ ኑራ እንድሪስ የሁለት ሴት እና የአንድ ወንድ ልጅ እናት ነበሩ፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም