በዓሉን በሰላም ለማክበር ዝግጅት መደረጉን የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስተዋቀ

72
ሐረር መስከረም 15 / 2012---የደመራና የመስቀል በዓል በደመቀና በሰላማዊ ሁኔታ እንዲከበር አስፈላጊ ዝግጅት ማድረጉን የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስተዋቀ። በዓሉን በድምቀት ለማክበር ከክልሉ የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የተለያዩ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ያመለከቱት ደግሞ የሐረር መካነ ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ቄስ መለከሰላም ጥበቡ መላኩ ናቸው ። የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ለታ በዳዳ ለኢዜእ እንዳሉት በክልሉ ነገ እና ከነገ በስቲያ የሚከበረው የደመራና የመስቀል በዓል በደመቀና በሰላማዊ መንገድ እንዲከበር ፖሊስ አስፈላጊውን ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል። በተለይ በደመራ በዓል የጸጥታ ችግር እንዳይከሰት በበዓሉ ስነ ስርዓት ላይ መከናወን ስለሚገባው የጸጥታ ስራ የክልሉ ፖሊስ ከተለያዩ የክልሉና የፌደራል ጸጥታ አካላት እንዲሁም የቤተክርስቲያኗን ተወካዮች ባሳተፈ የጋራ የጸጥታ እቅድ በማውጣት ዝግጅት ማድረጉን አስረድተዋል። ከዚህ በተጨማሪ የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት፣ ወጣቶች፣ የክልሉ የሰላም አምባሳደርና ሌሎች ተባባሪ አካለት በበዓሉ ስነስርዓት ላይ ሰላም የማስከበር ሥራ እንደሚያከናውኑ ነው የገለጹት። "ህዝበክርስቲያኑም በበዓሉ ወቅት የሚያጋጥሙ የወንጀል ድርጊቶችን ለፖሊስ ፈጥኖ በመጠቆም ወንጀልን በጋራ የመከላከል ስራ ማከናወን ይኖርበታል" ብለዋል ምክትል ኮሚሽነር ለታ። "የመስቀልና የደመራ በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባለፈ የተራራቁና ተጠፋፍተው የነበሩ ሰዎች የሚገናኙበት የተቀደሰ በዓል ነው" ያሉት ደግሞ የሐረር መካነ ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ቄስ መለከሰላም ጥበቡ መላኩ ናቸው። በዓሉ ከህዝበ ክርስቲያኑ ባለፈ የሌላ እምነት ተከታዮችና የውጭ አገር ዜጎች ጭምር የሚታደሙበትና የሀገሪቱን መልካም ገጽታ ለሌሎች የሚተዋወቅበት ደማቅ በዓል መሆኑን አስታውቀዋል። በዓሉ በቤተክርስቲያን ትውፊትና ትዕዛዝ መሰረት የሚከበር መሆኑን የጠቆሙት ቄስ መለከሰላም ጥበቡ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የበዓል ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል። የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክረውና በዩኔስኮ የተመዘገበውን የመስቀልና የደመራ በዓል በድምቀትና በሰላም ለማክበር ከክልሉ መስተዳድር የጸጥታ አካላት ጋር የተለያዩ ዝግጅቶች ሲያደርጉ መቆየታቸውንም አመልክተዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም