በአገራዊ ፍቅርና ስነ-ምግባር ዙሪያ ስልጠና የወሰዱ 70 እጩ ዲፕሎማቶች ተመረቁ

64
መስከረም 15/2012 በአገራዊ ፍቅርና ስነ-ምግባር ዙሪያ በሜጀር ጀነራል ኃየሎም አርአያ ወታደራዊ አካዳሚ ለአንድ ወር ስልጠና የወሰዱ 70 እጩ ዲፕሎማቶች ተመረቁ። እጩ ዲፕሎማቶቹ በአንድ ወር ቆይታቸው ስለ አገር ፍቅርና አርበኝነት፣ ተቋማዊ ባህል በተጨማሪም ወታደራዊ ሥነ-ልቦና እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ባህልና ስነ-ምግባር ዙሪያ ሰልጥነዋል። የሜጀር ጀነራል ኃየሎም አርአያ ወታደራዊ አካዳሚ ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ታደሰ መኩሪያ  ሥልጠናው ስኬታማ እንደነበር ነው የገለጹት። በሥልጠናውም እጩ ዲፕሎማቶቹ ጥሩ ሥነ-ምግባርና የተሻለ ክህሎት አገኝተው በቀጣይ የስራ ዘመናቸው ውጤታማ እንዲሁኑ ያግዛቸዋል ብለዋል። እጩ ተመራቂዎቹም በተወካያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት ከሥልጠናው አገራቸውንና ህዝባቸውን ለማገልገል ለቀጣይ ሥራቸው ጠቃሚ ግብዓት ማግኘታቸውን ተናግረዋል። የእጩ ዲፕሎማቱ ተወካይ ዘሪሁን ብርሃኑ እንደተናገረው የአገረ ፍቅር፣ መከባበርና ሌሎችም ጠቃሚ እሴቶችን በስልጠናው ወቅት መቅሰማቸውን ገልጿል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂሩት ዘመነ የእጩ ዲፕሎማቶቹ ሥልጠና በቀጣይ ህይወታቸው የህዝብ አገልጋይ፣ ታማኝ ዜጋና ቆራጥ ዲፕሎማት እንዲሆኑ ያግዛቸዋል ብለዋል። የወሰዱት ሥልጠና ከዘረኝነት፣ ከኃይማኖትና የፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ሆነው ሕዝብንና አገርን በቅንነት ለማገልገል የሚያስችላቸው መሆኑንም እንዲሁ። እጪ ዲፕሎማቶቹ እነዚሀን ባህሪያት ተላብሰው በቀጣይ ሥራቸው ላይ በማንጸባረቅ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንደሚወጡ ያላቸውን እምነትም ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል። የተመረቁት እጩ ዲፕሎማቶች በቀጣይ ለአንድ ዓመት በመሰረታዊ የዲፕሎማትነት ኃሳብና ተግባራት ላይ ተጨማሪ ሥልጠና ይሰጣቸዋል ተብሏል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም