ግጭት ለመፍጠር የሚሞክሩ ኃይሎችን ለህግ አጋልጠን እንሰጣለን-- የኢታንግ ልዩ ወረዳ ነዋሪዎች

40
ጋምቤላ (ኢዜአ) መስከረም 14 ቀን 2012  በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳ በህዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን ለህግ አጋልጠው እንደሚሰጡ ነዋሪዎቹ ገለጹ። ህዝቡ የአካባቢውን ሰላም ነቀቶ በመጠበቅ በክልሉ ለተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች መሳካት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስገነዝበዋል። በክልሉ ኢታንግ ልዩ ወረዳ ሲካሄድ የቆየው የሰላምና የልማት ህዝባዊ ኮንፈረንስ ባለ 7 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል። የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች በአቋም መግለጫቸው እንዳስታወቁት በወረዳው ህዝቡን እርስ በርስ በማጋጨት የግል ጥቅማቸውን ለማሳካት የሚነቀሳቀሱ ፀረ- ሰላምና ልማት ኃይሎች ለህግ እንዲቀርቡ በማድረግ በኩል የድርሻቸውን ለመወጣት ቃል ገብተዋል። በወረዳው ብሎም በክልሉ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ እንዳይቀለበስ ለአካባቢያቸው ዘላቂ ሰላምና ልማት በትኩረት እንደሚሰሩም በአቋም መግለጫቸው አመልከተዋል። በወረዳው ተቻችሎና ተደጋግፎ አብሮ የሚኖረውን ህዝብ በመከፋፈል የግል ጥቅማቸውን ለማሳካት የሚሞክሩ የጥፋት ኃይሎችን እንደሚታገሉም ነው ነዋሪዎቹ የገለጹት። በወረዳው ብሎም በክልሉ ዘላቂ ሰላም፣ ልማት፣ የህግ የበላይነትና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍንም ከመንግስት ጎን ሆነው የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ እንደሆኑም አመልክተዋል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው "ህዝብ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚቻለው የተረጋጋ ሰላም ሲፈጠር ነው" ብለዋል። በመሆኑም የወረዳው ህዝብ የአካባቢውን ሰላም ነቀቶ በመጠበቅ ለተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች መሳካት ጠንክሮ እንዲሰራ አሳስበዋል። "በወረዳው ህዝቡን በማጋጨት የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚሞክሩ ጸረሰላም ኃይሎች አሉ" ያሉት አቶ ኡሞድ፣ ህብረተሰቡ እነዚህን ኃይሎች ለህግ አጋልጦ እንዲሰጥ ጠይቀዋል። ህዝቡ አንድነቱን በማጠናከር በወረዳው ብሎም በክልሉ ባለው ሰፊ የተፈጥሮ ሃብት ተጠቃሚ ለመሆን ጠንክሮ መስራት እንዳለበት የገለጹት ደግሞ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተንኳይ ጆክ ናቸው። በክልሉ ሰፊ የመሬት፣ የውሃና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች ቢኖሩም በሚፈጠሩ የሰላም ችግሮች በተፈለገው ደረጃ ጥቅም ላይ እየዋሉ አለመሆናቸውን ገልጸዋል። በመሆኑም ህዝቡ ካለፉት ችግሮች ተምሮ ሰላሙን በማስጠበቅ ለልማት መነሳት እንዳለበት አሳስበዋል። በወረዳው ላለፉት ሦስት ቀናት በተካሄደው የሰላምና የልማት ህዝባዊ ኮንፈረንስ ላይ የክልልና የወረዳ አመራር አካላት ጨምሮ ከ250 በላይ የወረዳው ነዋሪዎች መሳተፋቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም