በሐረሪ ክልል የኮሌራ /አተት/ በሽታን ለመከላከል እየተሰራ ነው

72
መስከረም 14/2012 በሐረሪ ክልል የታየውን የኮሌራ /አተት/ በሽታ ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታወቀ፡፡ በቢሮው የህብረተሰብ ጤና ላብራቶሪ ምርምርና ድንገተኛ አደጋዎች ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ቱፋ እንደገለጹት በክልሉ በሽታው ከሐምሌ  ወር 2011  ጀምሮ  ምልክቱ ታይቷል፡፡ በሐምሌና መስከረም ወር ላይ በክልሉ የበሽታው  ምልክት ታይቶባቸው ምርመራ ከተደረገባቸው 27  ሰዎች መካከል በ11 ላይ በሽታው  ሙሉ ለሙሉ ሊገኝ መቻሉን ተናግረዋል። በሽታው የተከሰተባቸውን ስፍራዎች በመለየት ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት በሽታው ወደ ሌላ አካባቢ  እንዳይዛመት የመከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በበሽታው ለታያዙ ሰዎችም በከተማው አሚር ኑርና በገጠር ደግሞ ሶፊ ጤና ጣቢያ ውስጥ በተዘጋጁ የተለየ የህክምና ስፍራ ህክምናና የተለያዩ  የድጋፍና እንክብካቤ አገልግሎት እያገኙ ወደ መጡበት አካባቢ በመመለስ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ አስፈላጊ የሆኑ የህክምና ቁሳቁስና ባለሞያዎችን በየጤና ተቋማቱ ላይ  በማሟላት በሽታውን የመቆጣጠር ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም አቶ እሸቱ ጠቁመዋል፡፡ ህብረተሰቡም የአካባቢና የግል ንዕህናን መጠበቅና ውሃን አክሞ መጠቀም እንደሚገባ ገልፀው የበሽታው ምልክት ሲያጋጥምም ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ህክምናውን በነጻ ማግኘት እንደሚችሉ ተናግረዋል። ''ከሆስፒታሎችም ሆነ ከጤና ጣቢያ የሚላኩትን ኮሌራና ኮሌራ መሰል በሽታዎችን እየተመለከትንና ለሁሉም ህሙማን የህክምና አገልግሎት እየሰጠን እንገኛለን'' ያሉት ደግሞ በአሚር ኑር ጤና ጣቢያ የኮሌራ ህክምና መስጪያ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ቃለአብ ግርማ ናቸው፡፡ በሽታው አሁንም በመታየት ላይ መሆኑን የገለፁት ዶክተር ቃለአብ በአካባቢው እየጣለ የሚገኘው ከፍተኛ ዝናብ እና በሽታውን ለመከላከል በአካባቢና በግል ንጽህና አጠባበቅ ላይ ህብረተሰቡ የሚያከናውነውን ስራ ላይ ትኩረት አለመስጠቱ በሽታው እንዳይጠፋ ማድረጉን ተናግረዋል። አሁንም ቢሆን ህብረተሰቡ ውሃን አክሞ መጠጣት፣ የግልና የአካባቢን ንጽህና አጠባበቅን ማጠናከር እንዲሁም  የአትክልትና የፍራፍሬ ምርት አጥበው እንዲመገቡ የጤና ባለሞያዎችና የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ቤት ለቤት እየሄዱ ትምህርት በመስጠት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም