ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም በሰብል አሰባሰብ ወቅት የሚደርሰውን የምርት ብክነት ለመቀነስ እየተሰራ ነው

155
መስከረም 14/2012 በኢትዮጵያ በየዓመቱ በሰብል አሰባሰብ ወቅት የሚደርሰውን የ25 በመቶ የምርት ብክነት ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ለመቀነስ እየሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስረታወቀ። በኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጉድለት በየዓመቱ ከሚመረተው አጠቃላይ የምርት መጠን 70 ሚሊዮን ኩንታል ይባክናል ። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከምታገኘው አጠቃላይ ምርት ውስጥ 25 በመቶ ምርት ጥቅም ላይ ሳይውል ይባክናል። ለብክነቱ አይነተኛ ምክንያት ከሰብል አሰባሰብ ጀምሮ ምርቱ ጥቅም ላይ እስከሚውል ድረስ ዘመናዊ አሰራርን ባለመከተል መሆኑን ጥናቶች ያመላክታሉ። በአገሪቱ ባለፉት አራት ዓመታት የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የምርት ብክነት መጠን ከነበረበት 35 በመቶ ወደ 25 በመቶ ማውረድ ተችሏል። ይህም ሆኖ አሁንም በየዓመቱ 70 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ጥቅም ላይ ሳይውል ይባክናል። የግብርና ሚኒስቴር የብክነት መጠኑን እስከ 15 በመቶ ለመቀነስ የተለያዩ ተግበራትን እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል። በሚኒስቴሩ የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ለማ ለኢዜአ እንደገለጹት በአገሪቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ የሰብል አሰባሰብና አያያዝ ባለመኖሩ 25 በመቶ ምርት ለብክነት ይዳረጋል። አሁን ላይ ከምርት አሰባሰብ እስከ ማስቀመጥ የሚከሰተውን ብክነት ለማስቀረት ዘመናዊና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ መሆኑን አቶ ኢሳያስ ይናገራሉ። በአገሪቷ በአብዛኛው ሰብል ከመሰብሰብ ጀምሮ ምርትን ለገበያ እስከ ማቅረብ ወይም ጥቅም ላይ እስከሚውል ድረስ የሚከናወነው በበሬና በሰው ጉልበት መሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም በዚህ መካከል የሚደርሰውን ብክነት ለመቀነስ ሚኒስቴሩ ለአርሶ አደሩና ለነጋዴው የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨባጫዎችን እየሰጠ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። እንደ አቶ ኢሳያስ ገለፃ በተያዘው ዓመት የተሻለ የአየር ጸባይ በመኖሩ፣ የማዳበሪያ አቅርቦትና የተጠናከረ የቅድመ ዝግጅት ስራ በመከናወኑ የተሻለ ምርት ይጠበቃል። የሚገኘው ምርት በጥንቃቄ ተሰብስቦ ጥቅም ላይ እንዲውል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቁመዋል። ቀደም ሲል ይደርስ የነበረውን የምርት የብክነት መጠን ከ15 እስከ 20 በመቶ ለማድረስም ታስቦ እየተሰራ ነው። በዘንድሮው የሰብል መሰብሰቢያ ወቅት አርሶ አደሩ ኮምባይነርን በመጠቀም ምርቱን እንዲሰበስብና ብክነቱን እንዲቀነስ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተጠናቀዋል። በተለይ በአርሲና በባሌ አካባቢ ያለውን ቴክኖሎጂ የመጠቀም ልምድ ወደ ሌሎች ክልሎች በስፋት እንዲመጣ በማድረግ ብክነቱ እንዲቀንስ እየተሰራ ነው። አርሶ አደሩ በማህበር ተደራጅቶ የሰብል መሰበሰቢያ መሳሪያ እንዲገዛ የብድር አገልግሎት እንዲመቻችለትና ባለሃብቱም በኪራይ መሳሪያውን የሚያቀርብበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑ ተገልጿል። አጠቃላይ ከሚባክነው ምርት 25 በመቶ የሚሆነውን የሚይዘው በጎተራ ማስቀመጥ ሲሆን ይህም በገበያ እጦትና በሌሎች ምክንያቶች መሆኑም ታውቋል። በተለይ የቆሎና የማሽላ ምርትን ከሶስት ወር ጊዜ በላይ በጎተራ ማስቀምጥ ለተባይና ለብልሽት ያጋልጣል። ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት አርሶ አደሩ ምርቱን በአቅራቢያው ለገበያ የሚያቀርብበት የግብይት ቦታ እየተመቻቸ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ከተባይ የሚከላከልና ምርትን ሳይበላሽ ለረጅም ጊዜ ማቆየት የሚችል  ማዳበሪያ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብም እየተሰራ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም