የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች አልጋ ወራሽ ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አልናህያን ለይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ

89
አዲስ አበባ ሰኔ 8/2010 የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች አልጋ ወራሽ ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አልናህያን በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ ገብተዋል። አልጋ ወራሽ ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አልናህያን ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል። አልጋ ወራሹ አቀባበል ሲደረግላቸው ለክብራቸው ዘጠኝ ጊዜ መድፍ ተተኩሷል። ሰኔ 8 እና 9 ቀን 2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት የሚያደርጉት አልጋ ወራሽ ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አልናህያን በቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ከፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮችና አካባቢያዊ ሁኔታዎች ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሓማት ጋርም ውይይት እንደሚያደርጉ የሚጠበቁት አልጋ ወራሹ፤ በኢትዮጵያ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ይጎበኛሉ። የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ባለኃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን በተለያዩ መስኮች እያፈሰሱ ሲሆን በቀጣይም በግብርናና ቱሪዝም ዘርፍ ተሳትፏቸውን እንዲያጎለብቱ ይፈለጋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬቶች ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም