የኢድ አልፈጢር በዓል በደሴው ፉርቃን መስጊድ በድምቀት ተከበረ

64
ደሴ ሰኔ 8/2010 በደሴ ከተማና በአካባቢው በተለያዩ ኃይማኖቶች መካከል ለዘመናት የዘለቀውን ተከባብሮ የመኖር ባህል በማስቀጠል የኃይማኖት አባቶች የተጫወቱት ሚና የላቀ መሆኑን የደሴ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡ 1439ኛው የኢድ አልፈጢር በዓል በደሴው ፉርቃን መስጊድ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ምእመናን በተገኙበት በደማቅ ስነ ስርአት ተከብሯል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ደሳለኝ በላይ በበዓሉ ላይ እንደተናገሩት ደሴና አካባቢዋ በተለያዩ ኃይማኖቶች መካከል ተከባብሮ የመኖር ባህል የጎለበተባት የታላቋ ኢትዮጵያ መገለጫ ናት፡፡ ይህ ደግሞ በምክንያት የሚቃወም፣ በምክንያት የሚደግፍና ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ የሚፈልግ ህዝብ እንዲኖር ማድረጉን ነው ምክትል ከንቲባው የተናገሩት፡፡ በአካባቢው የመልካም አስተዳደር ችግሮችና የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለቶች የሚስተዋሉበት ቢሆንም ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የሚፈልግ ህዝብ በመፍጠር የኃይማኖት አባቶች ሚና የላቀ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ለዘመናት የዘለቀውን ተከባብሮ የመኖር ባህል በማስቀጠል የአገሪቱን ሰላምና አንድነት ማረጋገጥ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ የደሴ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ሊቀመንበር ሸህ ሰይድ ኡመር በበኩላቸው ''በኃይማኖት ለመኖርም ሆነ የፈጣሪን ትእዛዝ ለማክበር፣ የልማት ጥያቄን ለመመለስም ሆነ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ሰላም ወሳኝ ነው'' ብለዋል። ለዚህም ህዝበ ሙስሊሙ ከሌሎች የእምነት ተከታዮች ጋር በመሆን የአካባቢውን ጸጥታና ሰላም ማረግገጥ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ በዓሉን የተቸገረን በመርዳት፣ የታመመን በመጠየቅና ያዘነን በማጽናናት እንዲያከብር ጠይቀዋል፡፡ በደሴ ከተማ ሆጤ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ተስፋዬ እጀታ እምነታቸው ክርስትና ቢሆንም የእስልምና እምነት ተከታይ ከሆኑት ወላጅ እናታቸው ጋር በዓሉን በደስታ እንደሚያከብሩት ተናግረዋል፡፡ ''አካባቢው ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ቀድሞ የዘለቀበት ነው'' የሚሉት አቶ ተስፋዬ ማንም በእምነቱ ምክንያት የማይገለልበት፣ በልዩነት ውስጥ አንድ ሆኖ መኖር እንደሚቻል የሚያስተምርበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም