ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከልና ለማስወገድ የተቀረፀውን ፍኖተ ካርታ የማስተዋወቅ ስራ ተጀመረ

179
ኢዜአ መስከረም 13 / 2012 ዓ ም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከልና ለማስወገድ የተቀረፀውን ፍኖተ ካርታ የማስተዋወቅ ስራ በደሴ ከተማ ተጀምሯል። ለፍኖተ ካርታ ውጤታማ ትግበራም ሁሉም በቅንጅት እንዲሰራ ጥሪ ቀርቧል፡፡ የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከልና ለማስወገድ እንዲያስችል የተቀረፀውን ፍኖተ ካርታ ለማስተዋወቅ ያለመ መድረክ ባሳለፍነው ሳምንት በደሴ ከተማ ማካሄዱን ሚኒስቴሩ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። በትውውቅ መድረኩ በአማራ ክልል ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ጎልተው ከሚታይባቸው አምስት ዞኖችና 30 ወረዳዎች ለተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት በነሐሴ 2011 ዓ.ም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከልና ለማስወገድ የተቀረፀውን ፍኖተ ካርታ ይፋ መደረጉ የሚታወስ ነው። ከ2012 ዓ.ም ጀምሮም ለአምስት ዓመታት ተግባራዊ የሆነው ፍኖተ ካርታው በብሔራዊ ደረጃ የተዘጋጀ ሲሆን ፍኖተ ካርታው በዋናነት የሴቶችን ያለ እድሜ ጋብቻና ግርዛት ማስቀረትን አላማ ያደረገ ነው። የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር አማካሪ አቶ መብራቱ ይመር መንግስት በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀመውን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት በተለይም ደግሞ ያለ እድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛት የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት ለማስቀረት እየሰራ ነው ብለዋል። ይህንንም ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግስት እ.አ.አ 2025 ድርጊቱን ሙሉ በሙሉ ለማስቆም በለንደን በተካሄደው አለም አቀፍ መድረክ ቃል ኪዳን መግባቱን አስታውሰው ለተፈፃሚነቱም በርካታ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝም አስረድተዋል ፡፡ ከዚህም አንጻር በየአካባቢው ያሉ የሀይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ እድሮች፣ የጎሳ መሪዎች፣ የፍትህ አካላት፣ የትምህርት ቤት ክበባት፣ የሴቶች አደረጃጀቶችና ሌሎች ተፅእኖ ፈጣሪ አካላት ለፍኖተ ካርታው ትግበራ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል። ከመንግስታዊ መዋቅሩ ከሙያተኞችና ድርጊቱን ለመከላከልና ለማስወገድ በየደረጃው ከተቋቋሙ ጥምረቶች ጋር ተናቦ መስራት ከተቻለም የተፈለገውን ውጤት በአጭር ጊዜ ማምጣት እንደሚቻልም ነው አቶ መብራቱ የገለጹት። በፍኖተ ካርታው የተቀመጠው የጊዜ ማዕቀፍ ውስጥም ድርጊቱን መከላከልና ሙሉ በሙሉ ማስቆም እንዲቻል ሁሉም አካላት በቅንጅት እንዲረባረቡ የሚኒስትሯ አማካሪ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ በሴቶች ህጻናት ወጣቶች ሚኒስቴር የሴቶች ተሳትፎና ንቅናቄ ዳይሬክተር ስለሺ ታደሰ በበኩላቸው እስካሁን ድርጊቶቹን ለመከላከልና ለማስወገድ የሚያግዙ በርካታ ስራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ገልጸዋል። ሆኖም ከድርጊቱ አፈፃጸም ውስብስብነት፣ ከግንዛቤ እጥረት፣ ከቅንጅታዊ አሰራር መጓደል እንዲሁም ከመረጃ ክፍተት ጋር በተያያዘ የተፈለገው ውጤት ሊመጣ አለመቻሉን ገልፀዋል፡፡ በቀጣይ አምስት ዓመታት ከቤተሰብ ጀምሮ በሁሉም ደረጃ በተቀናጀ መልኩ ሊከናወኑ የሚገባቸውን ዝርዝር ተግባራት፣ የሚጠበቁ ውጤቶችንና የማስፈጸሚያ ስልቶችን በግልፅ የሚያመላክትና የድርጊት መርሃ ግብርን አካትቶ የያዘ ሰነድ ማዘጋጀት በማስፈለጉ የስነ-ህዝብና የጤና ዳሰሳ ሪፖርትና ሌሎች ጥናቶችን መሰረት በማድረግ ፍኖተ-ካርታው መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የሰነዱን አጠቃላይ ይዘት ለማስተዋወቅ የሚረዳ እንቅስቃሴ መጀመሩንና በቀጣይም እንደ የክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ ሰነዱ ተግባራዊ እንደሚሆንም አመልክተዋል፡፡ ከፍኖተ ካርታው በተጨማሪ በትውውቅ መድረኩ ላይ የአማራ ክልል የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መከላከል ጥምረት የ2011 ዓ.ም አፈፃፀም ሪፖርት በክልሉ የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ የተሳትፎና ንቅናቄ ዳይሬክተር አቶ ስማቸው ዳኜ ቋርቧል። የፋርጣና ላስታ ወረዳዎች ተወካዮችም ድርጊቱን በመከላከልና በማስቆም ረገድ ያከናወኗቸውን ተግባራት አስመልክቶ ያላቸውን ልምድና ተሞክሮም ዳይሬክተሩ ለመድረኩ ተሳታፊዎች አካፍለዋል። በተመሳሳይ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው የኤች.አይ.ቪ ስርጭት፣ በዜጎች በተለይም በሴቶች ላይ እያደረሰ ስላለው ጉዳት፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊትና ኤች.አይ.ቪ ስላላቸው ቁርኝት እንዲሁም ድርጊቱን መከላከልና ማስቆም የቫይረሱን ስርጭት በመግታት ረገድ ስለሚኖረው ጠቀሜታ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ተሰጥቷል። በመድረኩ በሴቶች ላይ አደጋና ጉዳት የሚያመጡ ማናቸውም ድርጊቶች በየትኛውም የኃይማኖት አስተምህሮ እንደሌለውና እንደሚወገዝ፣ ታዳጊ ሴቶች በእውቀት ላይ የተመሰረተ ምርጫና ውሳኔ እንዲያሳልፉ ማብቃትና እድል መስጠት እንደሚገባ፣ ጠቃሚ ልምዶችና ተሞክሮዎችን መቀመርና ማስፋት እንደሚያስፈልግም እንዲሁም፡፡ ለፍኖተ ካርታው ስኬታማ ትግበራ በየደረጃው የተቋቋሙ የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የመከላከል ጥምረቶችን እንቅስቃሴ በቅንጅታዊ አሰራር መደገፍና ይበልጥ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ እንዲሁም የሴቶች የልማት ቡድኖች ምዝገባና መልሶ የማደራጀት ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በተሳታፊዎች ስምምነት ላይ ተደርሷል። በቀረቡት ሰነዶች ዙሪያ ሰፊ ውይይት መደረጉንና ከተሳታፊዎች ለተሰጡ አስተያየቶችና ለተነሱ ጥያቄዎች የሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያ መሰጠቱን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በኢትዮጵያ ከ10 ልጃገረዶች መካከል 4ቱ የ18ኛ ዓመት ልደታቸውን ሳያከብሩ ትዳር እንደሚይዙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ያለእድሜ ጋብቻ ከሚፈጸምባቸው አምስት አገራት አንዷ እንደሆነችና በመላ አገሪቱ 15 ሚሊዮን ሴቶች ያለ እድሜያቸው ትዳር የያዙ መሆናቸውም እንዲሁ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም