የቡና ምርታማነትን በእጥፍ ማሳደግ ተቻለ

75
መስከረም 13/2012 በቡኖ በደሌ ዞን ባለፉት አምስት አመታት የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ለማስፋፋት የተሰራው ስራ ምርታማነትን በእጥፍ እንዳሳደገ የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ፅህፈት ቤት ገለፀ:: በቡኖ በደሌ ዞን ባለፉት አምስት አመታት የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ለማስፋፋት የተሰራው ስራ ምርታማነትን በእጥፍ እንዳሳደገ የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ፅህፈት ቤት ገለፀ፡፡ የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ፅህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ አቶ ልጃለም በፈቃዱ እንዳሉት ባለፉት አምስት አመታት ከጅማ ግብርና ምርምር ማዕከል የተገኙ ምርጥ ዝርያዎችን በ10 ወረዳዎች በአርሶአደሩ በስፉት እንዲተከሉ ተደርገዋል፡፡ በእነዚህ አመታት ከ257 ሚሊዮን 800ሺ በላይ ችግኞች በ77ሺ365 ሄክታር መሬት ላይ እንደተተከሉ ነው የገለፁት፡፡ የቡና ዝርያዎቹ በሄክታር እስከ 12 ኩንታል ምርት የሚሰጡ ሰባት አይነት ዝርያዎች እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡ ነባሩን ዝርያ በአዲስ በመተካት በተሰራው ስራ ከአምስት አመታት በፊት ሲገኝ የነበረውን ከ26ሺ ቶን የማይበልጥ አመታዊ ምርት ወደ 53ሺ600 ቶን እንዳሳደገ ነው የተናገሩት፡፡ በአማካይ በሄክታር አምስት ኩንታል የነበረው ምርታማነትም በአሁኑ ወቅት ሰባት ኩንታል መድረሱን ገልፀዋል፡፡ ከዞኑ በተጠናቀቀው አመት ከ12ሺ 980 ቶን በላይ የታጠበ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን የተናገሩት ምክትል ሀላፊው ይህም ከአራት አመት በፊት ከነበረው ከአምስት ሺህ ቶን በላይ ብልጫ እንዳለው አብራርተዋል፡፡ አርሶአደሩ ምርታማነቱ በማደጉ ምርቱን በራሱ ለገበያ ማቅረብ መጀመሩን ገልፀው፡፡ በዚህም ካለፉት ሁለት አመታት ወዲህ በበደሌ፣ ጮራ እና ዴዴሳ ወረዳዎች የሚገኙ 10 አርሶአደሮች ምርታቸውን በቀጥታ በምርት ገበያ በኩል ለገበያ ማቅረብ እንደጀመሩ አስታውቀዋል፡፡ በዞኑ ባለፈው ክረምትም በ11 ወረዳዎች ውስጥ ከ13 ሚሊዮን በላይ ምርጥ የቡና ችግኞች ከአራት ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ተተክለዋል፡፡ አርሶ አደር ዘይኑ ከማል በዞኑ ጮራ ወረዳ በልማቱ ከተሰማሩ አርሶአደሮች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ እሳቸው እንዳሉት ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ የተሻሻለውን የቡና ዝርያ በነባሩ በመተካት በየአመቱ ከአራት ሄክታር ማሳ እስከ 15 ኩንታል ምርት መሰብሰብ ጀምረዋል፡፡ አርሶአደሩ እንዳሉት ነባሩ ዝርያ ረጅም ዕድሜ ከማስቆጠሩ ጋር ተያይዞ በየአመቱ ፍሬ እንደማይሰጥ ገልፀው በአሁኑ ወቅት ግን መጠኑ ሳይቀንስ በየአመቱ እንደሚያፈራላቸው ተናግረዋል፡፡ ሌላኛው አርሶአደር ተፈሪ መኮንን በበኩላቸው አዲሱ የቡና ዝርያ የተሻለ ምርት ከመስጠቱም ባለፈ በቀላሉ በበሽታ ተጠቅቶ ፍሬው እንደማይረግፍ ተናግረዋል፡፡ ልማቱን ለማስፋፋት በሁለት ሄከታር ማሳ ላይ ነባሩን በአዲስ ዝርያ በመተካት ላይ እንደሚገኙ ነው የተናገሩት፡፡ በቡኖ በደሌ ዞን አስር ወረዳዎች በአሁኑ ወቅት ከ114ሺ 700 ሄክታር በላይ መሬት በቡና እየለማ ሲሆን ይህም ከዞኑ አጠቃላይ ሽፋን 19 ከመቶ እንደሆነ ነው የተገለፀው፡፡ በልማቱም ከ100ሺ በላይ አርሶአደሮች እየተሳተፉ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም