በምስራቅ አፍሪካ ዞን አራት ነጥብ ሁለት ውድድር እየተሳተፉ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ጥሩ ፉክክር እያደረጉ ነው

54
አዲስ አበባ ሰኔ 8/2010 በጅቡቲ እየተካሄደ የሚገኘው የምስራቅ አፍሪካ ዞን አራት ነጥብ ሁለት ውድድር ኢትዮጵያን ወክለው እየተሳተፉ የሚገኙት የቼስ ተወዳዳሪዎች ጥሩ ፉክክር እያደረጉ ነው። በአፍሪካ ቼስ ኮንፌዴሬሽን በየዓመቱ የሚዘጋጀው ውድድር ከሰኔ 2 ቀን 2010 ጀምሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል። በወንዶች ፊዴ ማስተር አይዳኙም ግዛቸውና ለይኩን መስፍን ከተፎካካሪዎቻቸው ጋር ጠንካራ ፍልሚያ እያደረጉ ነው። የዓለም አቀፋ ቼስ ፌዴሬሽን ፊዴ ማስተር አይዳኙም ግዛቸው እስካሁን ባደረጋቸው ሰባት የዙር ጨዋታዎች አራቱን አሸንፎ፣ ሁለት አቻ እና አንዴ ተሸንፎ አምስት ነጥብ በመያዝ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ፊዴ ማስተር አይዳኙም በደረጃ ከሚበልጡት ከግብጽ የቼስ ግራንድ ማስተሮች ሄሻም አብዱራህማንና ፋውዚ አድሃም ጋር ባካሄደው ጨዋታ አቻ በመውጣት ድንቅ ብቃቱን ማሳየቱን የኢትዮጵያ የቼስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይፈ በላይነህ ለኢዜአ ገልጸዋል። ሌላኛው የቼስ ተወዳዳሪ ለይኩን መስፍን እስካሁን ባደረገው ሰባት ጨዋታ አራት ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ ሁለት ተሸንፎ አንድ ጊዜ አቻ በመውጣት 4 ነጥብ 5 ነጥብ በመያዝ አምስተኛ ደረጃን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። የግብጽ የቼስ ግራንድ ማስተር ሄሻም አብዱራህማን በስድስት ነጥብ አንደኛ ሲሆን፤ ሌላኛው የግብጽ የቼስ የግራንድ ማስተር ፋውዚ አድሃምና የኡጋንዳው በተመሳሳይ አምስት ነጥብ በመያዝ ባላቸው የቼስ ተጫዋችነት ደረጃ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። በሴቶች ልደት አባተ እስካሁን ባደረገችው አምስት ጨዋታዎች ሁለት አሸንፋ ሁለት ተሸንፋ አንድ ጊዜ አቻ ወጥታ ሁለት ነጥብ አምስት ነጥብ ሰብስባ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ሌላኛዋ ተወዳዳሪ ፌቨን ገብረመስቀል እስካሁን ባደረገችው አምስት ጨዋታዎች አንድ አሸንፋ አንድ አቻ ወጥታ ሁለት ተሸንፋ አንደ ነጥብ አምስት ነጥብ በማግኘት አራተኛ ደረጃን ይዛለች። በሁለተኛ ዙር ፌቨን ገብረ መስቀልና ልደት አባተ እርስ በእርስ ያደረጉት ጨዋታ በአቻ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል። የግብጾቹ የቼስ ግራንድ ማስተሮች ሞታዝ አያህ አራትና ኢላንሳሪ ኤማን ሦስት ነጥብ በማስመዝገብ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል። በቀጣይ ቀናት የሚደረጉ የዙር ጨዋታዎች በሁለቱም ጾታዎች የሚያሸንፉትን ተወዳዳሪዎች እንደሚለይ ይጠበቃል። በቼስ የውድድር ህግ መሰረት የውድድር አሸናፊ የሚለየው የቼስ ተወዳዳሪው በዙር ከተጋጣሚዎቹ ጋር በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች በሚሰበስበው ነጥብና ባሸነፈው የጨዋታ ብዛት አማካኝነት ነው። አንድ ተወዳዳሪ አንድ ጨዋታ ሲያሸንፍ አንድ ነጥብ አቻ ሲወጣ ዜሮ ነጥብ አምስት ነጥብ ያገኛል። በውድድሩ በወንዶች ከአንድ እስከ ሶስት የሚወጡ ተወዳዳሪዎች የአንድ ሺህ፣ የ800 እና 600 ዶላር ሽልማት ሲያገኙ፤ ከአንድ እስከ ሶስት ለሚወጡት ሴቶች ደግሞ 750፣ 500 እና 250 ዶላር ይበረከታል። በሁለቱም ጾታዎች የሚያሸንፉ ተወዳዳሪዎች በ2018 የዓለም የቼስ የአገሮች ሻምፒዮና ላይ አፍሪካን ወክለው የመሳተፍ ዕድል ያገኛሉ። የምስራቅ አፍሪካ የዞን አራት ነጥብ ሁለት የቼስ ውድድር እስከ ሰኔ 12 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ይቆያል። ባለፈው ዓመት የምስራቅ አፍሪካ የዞን አራት ነጥብ ሁለት የቼስ ውድድር በጅማ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም