በአዲግራት መስቀል በዓልን በማስመልከት የተዘጋጀ የብስክሌት ውድድር ተጠናቀቀ

86
መቀሌ (ኢዜአ) መስከረም 12 ቀን 2012 በዓዲግራት ከተማ የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ የተካሄደ የብስክሌት ውድድር ዛሬ ተጠናቀቀ። በክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ወይዘሪት አበባ በሪሁ ለኢዜአ እንደገለጹት ከመስከረም 9 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በሁለቱም ጾታዎች በሰባት የስፖርት አይነቶች በተካሄደ ውድድር ከ200 በላይ ስፖርተኞች ተሳትፈዋል። በክለቦች በ35 ኪሎ ሜትር የከተማ ውድድር መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪነግ ፣ ትራንስ ኢትዮያጵና መሰቦ ሲምንቶ ፋብሪካ እንደየ ቅደም ተከተላቸው ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል። በወንዶች ኤ ኮርሶ 60 ኪሎ ሜትር የከተማ ውድድር ጉና ንግድ ስራዎች አክሲዮን ማህበር፣ ትራንስ ኢትዮጵያና መሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ይዘዋል። በሴቶች ማውንቴን የ20 ኪሎ ሜትር ውድድር መቀሌ 70 እንደርታ በተወዳዳሪዎቹ አማካኝነት ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ሊይዝ ችሏል ። በወንዶች 45 ኪሎ ሜትር ውድድር ደስታ የአልኾል መጠጥ ፋብሪካ፣ የዓዲግራት መጠጥ ውሃ አገልግሎትና ዓዲግራት ደንበስኮ  ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል። ሌሎችም በክለቦችና በግል የተካሄዱ የብስክሌት ውድድሮች ዛሬ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል ። በግልና በቡድን ከአንደኛ አስከ ሦስተኛ ደረጃ የያዙ ቡድኖችና የግል ስፖርተኞች የሜዳሊያና የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል። የእግርና መረብ ኳስ፣ የጠረጴዛ ቴኒስና የቅርጫት ኳስ ውድድሮች እንደቀጠሉ መሆኑን ወይዘሪት አበባ  አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም