የመቻቻልና የመረዳዳት ባህላዊ እሴቶች ለማጠናከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ የእስልምና እምነት ተከታዮች ገለጹ

188
ነገሌ /ፍቼ ሰኔ 8/2010 የመቻቻል፣ አብሮነትና የመረዳዳት ባህላዊ እሴቶች ለማጠናከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ በነገሌ እና በፍቼ ከተሞች ዛሬ በተከበረው የኢድ አልፈጥር በዓል ወቅት የእስልምና እምነት ተከታዮች ገለጹ በነገሌ ከተማ እግር ኳስ ሜዳ በተከበረው በዓል ተካፋይ የነበሩት አቶ አህመዲን ኮሬ እንዳሉት መረዳዳት፣ መከባበርና የታመሙን መጠየቅ በእስልምና ኃይማኖት ህግ የውዴታ ግዴታ ነው። አልፎ አልፎ በሚታዩ የአክራሪነት አስተሳሰቦች በሚፈጠሩ ግጭቶች አንዱ የሌላውን መመኘትና መቀማት በቅዱስ ቁርዓን ፍፁም የተከለከለና የሚወገዝ እንደሆነም ጠቅሰዋል። በአከባቢቸው ብሎም በሀገሪቱ የተለመደው የመቻቻል፤ የመረዳዳትና የመከባበር ባህል እንዲጎለብት በመደገፍ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡ ሌላው የበዓሉ ተሳታፊ አቶ ሰፊ ኢብራሂም በሰጡት አስተያየተ "የኢድ አልፈጥር በዓል ሲከበር በሀገሪቱ ሰላምና እድገት እንዲመጣ ለፈጣሪያችን ምስጋናና ፀሎት በማድረግ ሊሆን ይገባል" ብለዋል። የጉጂ ዞን ሸሪያ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሸክ ከድር አብዱረህማን  ለበዓሉ ታዳሚዎች ባስተላለፉት መልዕክት "አክራሪነትና ጽንፈኝነት የኃይማኖቱን አስተምሮ የሚጥስ ተገቢ ያልሆነ ተግባር ነው" ብለዋል። በኃይማኖቱ የተፈቀደና የታዘዘው መቻቻል፣ መረዳዳትና አብሮነት ጥንትም የነበረ አሁንም ያለ ወደፊትም የሚኖር የተከበረና የተመረጠ ባህል እንደሆነም ገልጸዋል። በተመሳሳይ በዓሉ የመረዳዳትና የመተጋጋዝ ባህልን በሚያንፀባርቅ ስነስርዓት በፍቼ ከተማ ሁለገብ ስታዲዮም በድምቀት ተከብሯል፡፡ በዓሉን በመተጋጋዝ፣ በመረዳዳትና በሰላማዊ ሁኔታ እያሳለፉ መሆናቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የእምነቱ ተከታዮች ተናግረዋል። ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል መምህር አማን ኢብርሂም እንዳሉት በሰላምና በእኩልነት መንፈስ በዓሉን በሰላማዊ ሁኔታ እያከበሩ ነው፡፡ በግላቸውም አቅመ ደካሞችን  በመርዳት የፆሙን ወቅት ማሳለፋቸውን ጠቅሰዋል። ሃጂ ኡስማን አብደላ በበኩላቸው እስልምና የሰላም፣ የፍቅርና የወዳጅነት እምነት እንደመሆኑ ይህን በሚያሳይ መልኩ በዓሉን በደስታ እያሳለፉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በኦሮሚያ የሰሜን ሸዋ ዞን እስልምና ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሼህ ሙራድ ሁሴን  በበዓሉ ስነ-ስርዓት ወቅት የእምነቱ ተከታዮችም ከበዓሉ በፊትና አሁንም አቅመ ደካሞችና ህሙማን በመርዳት በጎ ተግባር ማከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡ በበዓሉ ላይ የተገኙት የፍቼ ከተማ ከንቲባ ተወካይ አቶ ወሰና አበበ "በሀገሪቱ የኃየማኖት  እኩልነት ህገመንግስታዊ ዋስትና ተሰጥቶታል" ብለዋል። ይህም የእምነቱ ተከታዮችም ኃይማኖታቸውን በነጻነት እንዲገልጹ በማስቻሉ በግልም ሆነ በጋራ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም