የኢድ አልፈጥር በዓል በባህር ዳርና ደብረ ብርሃን ከተማ ተከበረ

80
ባህር ዳር / ደብረ ብርሃን ሰኔ 8/2010 ህዝበ ሙስሊሙ ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር ለዘመናት የቆየውን አብሮ የመኖርና የመተሳሰብ መልካም እሴት ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ ተባብሮ ሊሰራ እንደሚገባ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ገለፁ። አንድ ሺህ 439ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በሶላትና በስግደት ዛሬ በባህርዳር አፄ ቴዎድሮስ ስታዲየምና በደብረ ብርሃን ከተማ በድምቀት ተከብሯል። ፕሬዝዳንቱ ሸህ ሰይድ መሀመድ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ሙስሊሙ ህብረተሰብ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በማሰብ ሊሆን ይገባል። “በተለይ በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ አካባቢዎች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን መደገፍና መንከባከብ ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ነው'' ብለዋል። ከሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ጋር ለዘመናት በሰላም፣ በፍቅርና በመተሳሰብ አብሮ የመኖር መልካም እሴት ሳይበረዝ ተጠናክሮ ለትውልድ እንዲተላለም ህዝበ ሙስሊሙ ተባብሮ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ “ሀገራችን ኢትዮጵያ የተለያዩ ሃይማኖቶች ተቻችለውና ተከባብረው የሚኖሩባት ሀገር መሆኗ ልዩ ያደርጋታል'' ያሉት ደግሞ በበዓሉ ላይ የተገኙት የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አየነው በላይ ናቸው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የነበረውን አለመረጋጋት ወደቀደመው ሰላሙ እንዲመለስ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ለሰላሙ መከበር ከፍተኛውን ድርሻ ማበርከቱን ገልፀዋል፡፡ በባህርዳር ግንቦት 20 ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ አህመድ ሲራጅ በበኩላቸው “በዓሉን ስናከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በማሰብ ነው'' ብለዋል። የፋሲሎ ክፍለ ከተማ ነዋሪው ወጣት ከድር አሊ በበኩሉ “ታላቁን ረመዳንን ከአልባሌ ቦታ በመራቅ በፆምና በፀሎት እንዳሳለፈን ሁሉ በዓሉን ስናከብርም የተቸገሩትን በመጠየቅ መሆን አለበት'' ብሏል። በተመሳሳይ ይኸው በዓል በደብረ ብርሃን ከተማ በታላቅ ኃይማኖታዊ ሰነ ስርዓት ዛሬ ተከብሯል፡፡ በበዓሉ ላይ የተገኙት የሰሜን ሽዋ ዞን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሸህ ሙሃመድ ዘይን ሷሊህ “ህዝበ ሙስሊሙ የመልካም ስነምግባር እሴቶችን በመጠበቅ ለአካባቢያዊ ልማት መስራት ይገባዋል'' ብለዋል። የእስልምና እምነት ተከታዮች በፆም ወቅት ሲያበረክቱት የነበረውን መልካም ተግባራት አጠናክረው በመቀጠል ለሰላምና ልማት ስራዎች መጠናከር አበክረው ሊሰሩ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ በተለይም ወጣቶች የመልካም ስነምግባር እሴቶችን በመጠበቅ ከሌሎች እምነት ተከታዮች  ጋር በመሆን በተጀመሩ የልማት ስራዎች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡ በዓሉ በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች በሶላትና በስግደት ተከብሮ ውሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም