የሃድያ ህዝብ በኢትዮጵያውነቱ አይደራደርም-- የሆሳዕና ነዋሪዎች

77
መስከረም 12/2012 የሃድያ ህዝብ ሰላሟና አንድነቷን የጠበቀች ኢትዮጵያን የማስቀጠሉ ሃላፊነት የህልውናው ጉዳይ አድርጎ እንደሚወስደው የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦቸና ህዝቦች ክልል በመገኘት ከሆሳዕና ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል። "የኢትዮጵያ አንድንትና ሰላም ጉዳይ" ደግሞ በውይይቱ ተሳታፊዎች በዋናነት የተነሳ ሃሳብ ነው። የሃድያ ህዝብ ከሌሎች ህዝቦች ጋር ተከባብሮ በመኖር ረገድ  ዘመናትን የተሻገረ ታሪክ እንዳለው ነው ተሳታፊዎቹ አጽኖት ሰጥተው የተናገሩት። በመሆኑም የሃድያ ህዝብ የብሄር ብሄረሰቦች መብት የተከበረባት እንዲሁም ሰላሟና አንድነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያን እውን የማድረጉን ጉዳይ እንደማይደራደርበትም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የመቀጠልም ሆነ የመፍረስ  ጉዳይ በግለሰቦች ፍላጎት እንደማይሳካ በማከል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በምላሻቸው "በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ ቁርሾዎች ቢኖሩ እንኳ  አስተምረውን ሊያልፉ እንጂ ዘመን ተሻግረው ሊያለያዩን አይገባም" ብለዋል። ይቅርታ ማድረግ በጋራ ለመሻገር ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አንስተው፤ የሃድያ ህዝብ ይህን በተግባር ማስተማር በመቻሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ማንኛውንም አይነት የመሰረተ ልማትም ሆነ የአስተዳዳር ጥያቄ "አገር ከማስቀጠል" በታች በመሆኑ አገር ሲኖር የሚከወን መሆኑንም አብራርተዋል። ይህ መሆን ካልቻለ ግን ሁሉም ነገር 'ቤትን አየር ላይ እንደመገንባት ይሆናል' ነው ያሉት። የሃድያ የአገር ሽማግሌዎች ወጣቱ ትውልድ ባህሉንና አገሩን አውቆ እንዲያድግ ማስተማር እንደሚገባቸውም ጠቅላይ ሚንስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም