አዴፓ ከነገ ጀምሮ በፖለቲካና በልማት ጉዳዮች ላይ ይመክራል

92
ባህር ዳር መስከረም 12 / 2012  የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) በፖለቲካና በልማት ጉዳዮች የሚመክር ስብሰባ ከነገ ጀምሮ እንደሚያካሂድ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በጽህፈት ቤቱ የህዝብ አደረጃጀት ኃላፊ አቶ አብርሃም አለኸኝ ለኢዜአ እንደገለጹት በስብሰባው ከ2 ሺህ 500 በላይ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ እስከ ወረዳ ድረስ ያሉ አመራሮች ይሳተፋሉ። ለሦስት ቀናት በሚቆየው ስብሰባ ያለፈውን ዓመት የፖለቲካና የድርጅት ስራዎች የእቅድ አፈፃፀም ይገመገማል። ያገጠሙ ችግሮችና የተወሰዱ መፍትሄዎች ይታያሉ ብለዋል። በተለይም ባጋጠሙ ችግሮችና ችግሮችን ለመፍታት የተሄደውን ርቀት በጠንካራና ደካማ ጎን ተለይቶ ይቀርባል። ውይይትም ይደረግበታል።ለቀጣይም የእቅዱ አካል ሆኖ እንደሚታይም አመልክተዋል። እንዲሁም በ2012 የድርጅትና የልማት ስራዎችን እቅድና የማስፈፀሚያ ስልቶች ቀርበው አመራሩ በሚያደረገው ውይይት ዳብሮ የእቅዱ አካልም ይሆናል ብለዋል። በተለይም የክልሉን ሰላምና ደህንነት በማረጋገጥ፣ የወጣቶችን የስራ እድል ፈጠራ ፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ስራዎች ዋነኞቹ የመወያያ አጀንዳዎች መሆናቸውን ገልጸዋል። እንዲሁም የግብርና ልማትና የኢንቨስትመንት እቅዶች ቀርበው ቀጣይ አቅጣጫ  እንደሚቀመጥ አቶ አብርሃም አብራርተዋል። ስብሰበው  በቀጣይ በቡድንና በጋራ  ውይይት ይደረግባቸዋል ብለዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም