በጋምቤላ ክልል እድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ 26 ሺህ የሚሆኑ ህጻናት ወደ ትምሀርት ቤት ይመጣሉ

81
ጋምቤላ ኢዜአ መስከረም 11 / 2012 ዓም  በጋምቤላ ክልል በተያዘው የትምህርት ዘመን እድያቸው ለትምህርት የደረሱ 26  ሺህ የሚሆኑ ህጻናት ወደ ትምህርት ቤት ይመጣሉ፡፡ የቢሮው ምክትል ኃለፊ አቶ ኮንግ ጆክ ለኢዜአ እንደገለጹት ህጻናቱን ወደ ትምህርት ቤት ለማምጣት የቅስቀሳና የምዝገባ ስራዎች ተከናውኗል ። በትምህርት ዘመኑ ትምህርትን ተደራሽ ከማድረግ ጎን ለጎን ግብአቶችን በሟሟላት ጥራትን ለማስጠበቅ በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል ። ባለፈው ዓመት እንደ ጉድለት የታዩትን የመምህራን ስብጥርና የእቅም ማነስ ችግሮች ለመፍታት እንደሚሰራም ጠቁመዋል። በትምህርት ዘመኑ ለትምህርት ልማት እቅድ መሳካት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተለይም ወላጆች ተሳትፎአቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል። የባለድርሻ አካላት በበኩላቸው በትምህርት ዘመኑ ለተነደፈው እቅድ ስኬት ጠንክረው ለመስራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። ከባለድርሻ አካላት መካከል መምህር አበራ ዳመና በሰጡት አስተያየት ባለፈው ዓመት በተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች በርካታ የትምህርት ስራዎች ሲባክኑ እንደነበር ጠቅሰዋል። በተያዘው የትምህርት ዘመን ለተማሪዎች ውጤትና ለትምህርት ጥራት መሻሻል ጠንክረው ለመስራት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል። በዘንድሮው ዓመት ከመምህራንና ሌሎች አካላት ጋር በመሆን ለትምህርት ስራዎች መሻሻል በትኩረት እንደሚሰሩ የተናገሩት ደግሞ የክልሉ የወላጅ መምህራን ህብረት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ኡቦንግ ኡርያሚ ናቸው። በተለይም ከቀበሌዎች ስልጠና ቦርድና ወላጆች ጋር በመሆን የተጠናከረ ክትትል በማድረግ የተማሪ መውደቅና ማቋረጥን ለመቀነስ እንደሚሰሩ አመላክተዋል። ከተማሪ ወላጆች መካከል አቶ ሰለሞን ታደሰ በበኩላቸው "የትምህርት ስራ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው መንግስት፣ መምህራንና ወላጆች በቅንጀት መስራት ሲችሉ ነው" ብለዋል። በክልሉ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን በቅድመ መደበኛ፣ በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም በመሰናዶ ትምህርት ቤቶች ከ142 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት መደረጉን ታውቋል ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም