ሰላሟ የተጠበቀ ኢትዮጵያን እውን ማድረግ የሁሉም ነገር መሰረት ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

61
መስከረም 11/2012 በዜጎች የሚነሱ የልማት ጥያቄዎችን እውን ማድርግ የሚቻለው በቅድሚያ ሰላሟ የተጠበቀ ኢትዮጵያን መፍጠር ሲቻል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሃዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ በመገኘት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አድርገዋል። በውይይቱ ወቅት ከነዋሪዎቹ ሰላምን፣ ልማትን እንዲሁም አገራዊ አንድነትን የተመለከቱ ጥያቄና አስተያየቶች ተነስተዋል። የመንገድ፣ የሆስፒታልና የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማትና ሌሎችም መሰል ጥያቄዎች ከተሳታፊዎች ተነስተዋል። በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የዞኑ ተወላጆችን ወክለው በውይይቱ ላይ የተገኙ አንድ ተሳታፊም የዞኑ ተወላጆች ወደ አገራቸው ገብተው እንዲሰሩ እድል እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው የሃድያ ህዝብ ሰላምን በመጠበቅ ረገድ አኩሪ ታሪክ እንዳለው አንስተው ይህ መልካም የህዝብ ተሞክሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎች መስፋት አለበት ብለዋል። የኢትዮጵያ ህዝቦች የተሳሰረ ማንነት እንዳላቸው ገልጸው በተለያዩ ጊዜያት የተፈጠሩ ቅራኔዎች ቢኖሩ አንኳን በይቅርታ ማለፍ እንደሚገባም ገልጸዋል። በስፍራው የተገኙ ሚኒስትሮችና የመንግስት የስራ ሃላፊዎችም ከተነሱ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች መካከል የሚመለከታቸውን ወስደው ጥያቄዎችን ለመመለስ እንዲሰሩም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል። ደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች በተናጥል ሳይሆን በጋራ ኩባንያ በሟቋቋም በአገራቸው ቢሰሩ አዋጭ ነው ሲሉም ጠቁመዋል። መሆኑንም ለዚህ ስኬት መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍና እግዛ እንደሚያሰደርግ አረጋግጠዋል። በውይይቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን፣ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን. እና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም