"በኢትዮጵያ ተስፋም ስጋትም እየተስተዋለ በመሆኑ ሁላችንም ልናስብበት ይገባል---ምሁራን

57
መስከረም 11/2012 "በኢትዮጵያ ተስፋም ስጋትም እየተስተዋለ በመሆኑ ሁላችንም ከወዲሁ ልናስብበት ይገባል" ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ተናገሩ። "ኢትዮጵያ ከ40 ዓመታት በላይ ከአንድነት ይልቅ መለያየትን የሚያቀነቅኑና የሚከፋፍሉ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ነበሩባት" ይላሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰብአዊ መብትና የፌዴራሊዝም መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ መንግስቴ። በተለይም ላለፉት 27 ዓመታት ኢህአዴግ ያመጣቸው የራሱ ጥሩ ነገሮች ቢኖሩም ቋንቋን፣ብሄርንና ዘር ተኮር ፖለቲካ ላይ ማትኮሩ አሁን ለሚስተዋለው ፖለቲካዊ ችግር መንስኤ ሆኗል ይላሉ። ይህንንም ተከትሎ በህዝቡ ግፊት በአገሪቱ የፖለቲካ ለውጥ መምጣቱና ይህም እውነተኛ ዴሞክራሲን ለመገንባትና ሁሉን አቀፍ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ያስችላል የሚል ተስፋ አሳድሯል ብለዋል። ሆኖም የፖለቲካ ላውጡ እያመጣው ካለው ተስፋና ተጨባጭ ተግባራት ባሻገር ቀስ በቀስ የተለያዩ ፈተናዎች እየገጠሙት መሆኑን ያምናሉ። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ተስፋና ስጋት በተቀላቀለበት ሁኔታ እየተጓዘች መሆኑን ይናገራሉ። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአገራዊና አንድ ከሚያደርጉ የጋራ እሴቶች በተቃራኒ በብሄር ላይ መጠመድ ትልቁ ችግር ሆኗል ይላሉ። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ ከተደረገ ማግስት ጀምሮ በውጭ የሚኖሩ የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ፓርቲዎች፣ መገናኛ ብዙሃን፣ ግለሰቦችና ድርጅቶች በሰላም አገራቸው እንዲገቡና ለአገራቸው እንዲሰሩ መደረጉ የለውጡ ተጨባጭ ፍሬ መሆኑም ጠቅሰዋል። ይሁን እንጂ ለውጡ ያመጣውን ዴሞክራሲያዊ መብት እንዲሁም የመናገርና ሌሎች ነፃነቶችን በአግባቡ ከመጠቀም አኳያ ችግር ይስተዋላል። በመንግስት በኩልም ለውጡን በአግባቡ ከመምራት አንፃር ድክመት መኖሩ ፈተና መሆኑንም ተናግረዋል። በተለይ በርካታ የመገናኛ ብዙሃን በነፃነት የመስራት ምቹ ሁኔታ ቢፈጠርላቸውም በጋራ ጉዳዮች ላይ ከመስራት ይልቅ በብሄር ተኮር አጀንዳዎች ላይ ተጠምደው ይታያሉ። ይህም አገሪቷን ሙሉ ለሙሉ ወደ ተስፋ ከመውሰድ ይልቅ ስጋት የታከለበት ጉዞ እንዲሆን አስችሎታል ብለዋል። በመሆኑም የመገናኛ ብዙሃኑ የፖለቲካ ነፃነታቸው፣ ኤዲቶሪያል ፖሊሲያቸው፣ አቅማቸውና አሰራራቸው መታየት አለበት ይላሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና የኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ሙላቱ አለማየሁ አንደሚሉትም ለአገሪቷ ሰላምና አንድነት የመገናኛ ብዙሃን ሚና ቀላል አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ወጥቶ ሌላ ሁሉን አሳታፊና በአንድነት ላይ ያተኮረ ርዕዮተ አለም ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል ሲሉም ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም መንግስት ለውጡን በትክክል ለማስቀጠል የህግ የበላይነትን ማስከበር ይጠበቅበታል። የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በአፋጣኝ መፍታትና በአጋር ፓርቲዎች መካከል የጋራ የሆነ ስምምነት ኖሮ በአንድነት መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል። እንደ ምሁራኑ ገለፃ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከብሄር አወቃቀር ወጥተው ለአገር የሚጠቅም አጀንዳ ይዘው መስራት አለባቸው። ፓርቲዎቹ የማይራራቅ ፖሊሲ ይዘው በተለያየ ፓርቲ በመጠራት ቁጥራቸውን ከማበራከት ወጥተው በተጠናከረ ሃሳብ መመራት ቢችሉም ሲሉ ምክረ ሃሳባቸውን አቅርበዋል። የመገናኛ ብዙሃኑም ከምንም በላይ አገራዊ አንድነትንና የጋራ እሴትን መሰረት አድርገው ቢሰሩ ሲሉ ምሁራኑ አሳስበዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም