በአማራ ክልል የሚስተዋለውን ድህነት ለመፍታት ሳይንሳዊ የምፍትሄ አማራጮቸን እናቀርባለን ---ምሁራን

68
መስከረም 11/2012 በአማራ ክልል የሚስተዋለውን ድህነት በዘላቂነት ለመፍታት ሳዊንሳዊ የመፍትሄ አማራጮችን በማቅረብ ህዝባዊ አደራውን እንደሚወጣ የአማራ ክልል የምሁራን መማክርት ጉባኤ አስታወቀ። " የአማራ ህዝብ የፍትህ፣ የነጻነት፣ የእኩልነትና የዴሞክራሲ ትግል ለጠንካራ ኢትዮጵያዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ ላለፉት ሁለት ቀናት በባህር ዳር ከተማ የተካሄደው ጉባኤ ባለ 9 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ትናንት ማምሻውን አጠናቋል። የመማክርት ጉባኤው ማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት የጉባኤው የቦርድ አባል ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ ጉባኤው ወቅታዊ ክልላዊና አገራዊ ጉዳዮች በማንሳት መምከሩን ገልፀዋል። በተለይም የወጣቱን የስራ እጥነት ችግር፣ የኑሮ ውድነትና ድህነትን በተቀናጀ አግባብ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ በእውቀት ላይ ተመስርቶ መፍትሄ እንዲሰጠው አቅጣጨዎች ተቀምጠዋል። እየገጠሙ ያሉ ችግሮች በሃገር ውስጥ ምሁራን እውቀት ባለመሰራቱ የተፈጠረ እንጅ ከሙሁራን የእውቀት አቅም  በላይ ሆነው የተከሰቱ ባለመሆናቸው ለመፍትሄው በጋራ ይሰራል ብለዋል። ምሁራን የችግሩን አሳሰቢነት ዘግይተውም ቢሆን ተረድተዋል ያሉት ዶክተር ፈንታ በቀጣይ ምክንያት ሳይፈለግ የእውቀት ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። ምሁራን የሚያቀርቡትን የለውጥ ሃሳብ ባለሃብቶች በስራ ፈጠራና ሌሎች ዘርፎች እንዲሰማሩ መንግስትም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ የምሁራን መማክርቱ ብርቱ ጥረት እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡ የምሁራን ድርሻ ሃገራዊ እውቀትን ከአለም አቀፍ ጋር በማገናዘብ ሳይንሳዊ የችግር መፍትሄ አቅጣጫዎችን ማመላከት በመሆኑ ለውጤታማነቱም ምሁራን ለመስራት ተዘጋጅተዋል ብለዋል። የመማክርት ጉባአው በሁለት ቀን ቆይታው በማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጥናት ላይ ተመርኩዞ የመከረ ሲሆን ባለ 9 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ትናንት ማምሻውን አጠናቋል። ጉባኤው ካስቀመጣቸው የአቋም መግለጫዎች መካከልም አሁን በስራ ላይ ያለው ህገ መንግስት በሁሉም ዘንድ ይሁንታ ያገኘ ሆኖ እንዲሻሻል በእውቀት በማገዝ የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ አመላክቷል። እንዲሁም እኩልነት፣ ብልጽግና፣ ፍትህ የሰፈነባት ኢትዮጵያ እንድትገነባ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ጉባኤው በቋም መግለጫው ጠቅሷል። ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የመማክርት ጉባኤ  ከሁለት ሺህ በላይ የአገር ውስጥና በውጪ ሃገራት የሚኖሩ ምሁራንና የሃይማኖት አባቶች፣ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈውበታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም