የቀደሙት ያቆዩትን የመረዳዳት ባህል ትውልዱ ሊያስቀጥለው እንደሚገባ ብጹ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ አሳሰቡ

174
መስከረም 11/2012 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ አባቶችና እናቶች ያቆዩትን የመረዳዳት ባህል ትውልዱ ሊያስቀጥለው እንደሚገባ አሳሰቡ። ብጹ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ይህንን ያሉት በችግር ላይ የሚገኙ ህጻናትን ለመደገፍ ያለመ የአንድነት ማህበር ምስረታ ላይ በመገኘት ባደረጉት ንግግር ነው። በዚሁ ወቅት እንዳሉትም የቀደሙ አባቶችና እናቶች በችግር ውስጥ ያሉ ህጻናትን በመርዳትና በመደገፍ ለወግ ለማዕረግ ማብቃታቸውን በማስታወስ የአሁኑ ተውልድም ለሌሎች መኖርን ተግባራዊ ማድረግ አለበት። በተለይ እንደ አገር በአንድ ወቅት የገጠመን የረሃብ ችግር ለመፍታት በወቅቱ የነበሩ የቤተክርስቲያኗ አባቶች የህጻናትና የቤተሰብ ጉዳይ ድርጅትን አቋቁመዋል። ከተቋቋመ 45 ዓመታትን ያስቆጠረው ይህ ድርጅት  ከ42 ሺህ የሚለቁ ህጻናትን አሳድጎ እራሳቸውን እንዲችሉ አድርጓል። ይህ በጎ ተግባር ትውልዱ እንዲያስቀጥለውና የቀደሙትን ፈለግ ተከትሎ የመረዳዳት ባህል እንዲያጎለብት ጥሪያቸውን አቅርበዋል። የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ቀሲስ ሳምሶን በቀለ እንዳሉትም ድርጅቱ በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ የቀድሞ አባቶችና እናቶች ያቆዩትን ያህል ህጻናትን የመርዳት ስራ እየሰራ አይደለም። ድርጅቱ ለችግር የተጋለጡ ሃይማኖትና ብሔርን ሳይለይ ኤርትራን ጨምር በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በ36 ቅርንጫፎች አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ተቋማት 18 ብቻ ሲሆኑ ችግረኛ ህፃናትን የመቀበል አቅማቸውም ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመዋል። ለዚህም እንደ ምክንያት ከተጠቀሱት ማካከል ለድርጅቱ ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርጉ የቆዩት ግሪክና መሰል አገራት የኦኮኖሚ ቀውስ ውስጥ መግባትና ሌሎችም አገሮች ከኢትዮጵያ በላይ ችግር ላለባቸው አገራት ድጋፉን  በማዛወራቸው መሆኑን ጠቁመዋል። ይህንን በጎ ተግባር ለማስቀጠል የቀድሞ አባላቶች በጋራ ይህንን ድርጅት ለመደገፍ የሚያስችል ማህበር በዛሬው ዕለት አቋቁመዋል። ብፁ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ለዚህ በጎ ተግባር መጠናከር ቤተክርስቲያኗ የበኩሏን እንደምትወጣ አረጋግጠዋል። የአሁኑ ትውልድም ይህንን በጎ ተግባር ለማስቀጠል አሻራውን እንዲያሳርፍ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም