በማእከላዊና ምእራብ ጎንደር ዞኖች ለማገኙ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

53
መስከረም 11/2012  በማእከላዊና ምእራብ ጎንደር ዞኖች ባለፈው አመት በተከሰተ ግጭት ትምህርታቸውን አቋርጠው ለቆዩ ተማሪዎች የሚውል ግምቱ አንድ ሚሊዮን ብር የሚያጣ የትምህርት ቁሳቁስ በድጋፍ ተሰጠ፡፡ የማእካለዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ መስፍን እርካቤ ለኢዜአ እንደተናገሩት የትምህርት ቁሳቁሱ ድጋፍ የተገኘው እኛ ለእኛ ከተባለ የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ በእርዳታ ካበረከታቸው የትምህርት ቁሳቁሶች መካከል የመማሪያ ደብተሮች፣ የማጣቀሻ መጻህፍት፣ እርሳስ፣ የመጫወቻ ኳሶችና ሌሎች የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ይገኙበታል፡፡ ከትምህርት ቁሳቁሶቹ ውስጥ ከፊሉ ባለፈው ዓመት በዞኑ ተከስቶ በነበረው ግጭት ምክንያት ትምህርታቸውን ላቋረጡ የጭልጋ፣ የላይ አርማጭሆ፣ ምስራቅና ምእራብ  ደንቢያ ወረዳዎች ለሚገኙ ከ60 ሺህ በላይ ተማሪዎች ይሰራጫል፡፡ ከፊሉ ደግሞ በምእራብ ጎንደር ዞን በተመሳሳይ በግጭቱ ለተፈናቀሉ ተማሪዎች የሚላክ መሆኑን ሃላፊው ተናግረዋል፡፡ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፉ በግጭቱ ምክንያት ንብረታቸው የወደመባቸው ቤተሰቦች ልቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ የነበረባቸውን ጭንቀት የሚያቃልል እንደሚሆን ተመልክቷል። የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ተወካይ አቶ ሮቤል አያልነህ በርክክብ ስነስርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የትምህርት ቁሳቁሱ የተገኙት ከድርጅቱ አባላትና በአዲስአበባ ከሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብ የተሰባሰበ ነው፡፡ ድርጅቱ የትምህርት ቁሳቁሶቹን በማሰባሰብ ሂደት ከፌደራል ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በትብብር ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም