በአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ከባድ ስርቆት ሲፈጽም የተያዘ ግለሰብ በ19 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ

136
አርባምንጭ ሰኔ 8/2010 በአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ከባድ ስርቆት ሲፈጽም ተይዟል የተባለ ግለሰብ በ19 ዓመት ጽኑ እስራት እንድቀጣ መወሰኑን የአርባምንጭ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ገለጸ። የፍርድ ቤቱ ዳኛ አቶ ዮናስ መርዕድ ለኢዜአ እንደተናገሩት ውሳኔው የተላለፈው ግለሰቡ ግንቦት 29 ቀን 2010 ወደ ዩኒቨርስቲው ግቢ ዘልቆ በመግባት የተማሪዎችን የትምህርትና የተግባቦት መሳሪያዎችን ይዞ ለመሰወር ሲሞክር እጅ ከፍንጅ በመያዙ ነው። የስርቆት ወንጀሉን ከመፈፀሙ በፊትም ከተማሪዎች ጋር ተመሳስሎ በመግባት አዳራሽ ውስጥ ምግብ መመገቡ ተገልጸዋል። ተከሳሹ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በተማሪዎች መኝታ ቤት አከባቢ ባለው ረጅም ዛፍ ላይ በመውጣት ማሳለፉን ተከሳሹ ለፍርድ ቤቱ በሰጠው ቃል  አረጋግጧል፡፡ ከዚያም ሁሉም ተማሪዎች መተኛታቸውን በማረጋገጥ ከዛፉ ላይ ወርዶ ወደ ተማሪዎቹ መኝታ ክፍል በመግባት ሶስት ቶሽባ ላፕቶፖችና ተንቀሳቃሽ ስልኮች አውጥቶ መደበቁን መዝገቡ ያስረዳል። በኋላም በድጋሚ ወደ ተማሪዎች መኝታ ቤት በመግባት የኮምፒዩተሮችና ተንቀሳቃሽ ስልኮችን የቻርጅ ኬብሎችን ሰብስቦ ሲወጣ በግቢ ፖሊሶች እጅ ከፍንጅ መያዙን ገልጸዋል። በዚህም ዐቃቤ ህግ በማግስቱ ግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም በከባድ ስርቆት ወንጄል በአምስት መዝገቦች ክስ በማደራጀት ለፍርድ ቤቱ ማቅረቡን ገልጸዋል። ፍርድ ቤቱ መዝገቡን ከመረመረ በኋላ ግለሰቡ ተግባሩን ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ከመያዙ በላይ ጥፉቱን በማመኑና መከላከል ባለመቻሉ ሰኔ አንድ ቀን 2010 በዋለው ችሎት ግለሰቡ በ19 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን ተናግረዋል። የፍርድ ቤቱ ዋና አቃቤ ህግ አቶ ተፈሪ ዋልዋ ስለ ውሳኔው ተጠይቀው በሰጡት አስተያየት "ውሳኔው አስተማሪ ነው" ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም