ማዕከሉ ገበያ ተኮር የአኩሪ አተርና የሱፍ ዝርያዎችን በማላመድ እያስተዋወቀ ነው

80
መስከረም 10/2012 የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል ገበያ ተኮር የሆኑ የአኩሪ አተርና የሱፍ ዝርያዎችን በጣቢያዎችና በአርሶአደሮች ማሳ የማላመድና የማስተዋወቅ ስራ እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ፡፡ ማዕከሉ በተመረጡ አርሶ አደሮች ማሳና በምርምር ጣቢያዎች ላለፉት ሁለት ዓመታት እንዲላመዱ ያደረጋቸውን “አፍጋትና ራሳ ብላክ “የተባሉ የአኩሪ አተርና የሱፍ ዝርያዎችን በመስክ አስጎብኝቷል፡፡ በዚህ ወቅት የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አዛናው እንደተናገሩት ለአካባቢው ስነ-ምህዳር ተስማሚ የሆኑት ዝርያዎቹ በሄክታር ከ25 እስከ 30 ኩንታል ምርት መስጠት የሚችሉ ናቸው፡፡ “ማዕከሉ በተያዘው ዓመት አኩሪ አተርን በቋራ ፣መተማ ፣ምዕራብ አርማጭሆና ጠገዴ ወረዳዎች የዘር ብዜትና የማስተዋወቅ ስራ እየከናወነ ይገኛል” ብለዋል፡፡ ሱፍን ጎረቤት ሱዳን በስፋት በማልማት ለአለም ገበያም ሆነ ለኢትዮጵያ እያቀረበች እንደምትገኝ ያመለከተ ዳይሬክተሩ “ተመሳሳይ መሬት እየለን ሰብሉን በስፋት ማልማት አልቻልንም “ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የአካባቢው አርሶአደሮች የሚጠቀሙት የሱፍ ዝርያ በሄክታር የሚሰጠው ምርት ከ8 ኩንታል እንደማይበለጥና ማዕከሉ የሚያላምደው ዝርያ ግን በሄክታር 24 ኩንታል ምርት መስጠት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ አኩሪ አተርንም በተመሳሳይ በአራቱ ወረዳዎች በ80 ሄክታር ሰርቶ ማሳያ ላይ የዘር ምንጭ ለማድረግ በአርሶ አደር ማሳ ጭምር የዘር ብዜት እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል። “የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል ምርጥ ዘርና የመዝሪያ ማሽን ድጋፍ አድርጎልኝ በሶስት ሄክታር ላይ የዘራሁት አኩሪ አተር ሰብሉ በጥሩ የእድገት ደረጃ ላይ ይገኛል” ያሉት ደግሞ የጠገዴ ወረዳ አርሶአደር አቶ ዘያድ ወርቁ ናቸው፡፡ ሰብሉ በሄክታር ከ25 እስከ 30 ኩንታል እንደሚሰጥ አምና በሙከራ ከዘሩት ጎረቤት አርሶ አደሮች ማየታቸውን አመልክተው” ዘንድሮ ካለማሁት መሬት ከ60 ኩንታል በላይ የአኩሪ አተር ምርት እጠብቃለሁ” ሲሉ ገልጸዋል። በጠገዴ ወረዳ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት አቶ አስማማው አዛናው በበኩላቸው ማዕከሉ ባደረገላቸው የዘርና የቴክኖሎጂ ድጋፍ ዘንድሮ ለዘር የሚውል በሁለት ሄክታር መሬት አኩሪ አተር ማልማታቸውን ተናግረዋል፡ በቀጣዩ ዓመት በስፋት ሰብሉን በማልማት ምርቱን ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለማቅረብ እንዳሰቡ ጠቁመዋል፡፡ “ግብርናውን ለማገዝ የሚረባረቡ አካላት በድህረ ምርት አያያዝና እሴት በመጨመር ላይ ብዙ ሰርተን ተጠቃሚ የምንሆንበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለብን” ያሉት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የቀድሞ ኃላፊ ዶክተር ቦሰና ተገኘ ናቸው፡፡ የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል በአኩሪ አተርና ሱፍ ላይ እያካሄደ ባለው የማላመድና የማስተዋወቅ ምርምር ስራ በአኩሪ አተር በ80 ሄክታር መሬት 39 አርሶአደሮችን በማሳተፍ ላይ ይገኛል፡፡ እንዲሁም “ራሻ ብላክ” በተባለው የሱፍ ዝርያ ደግሞ አራት አርሶአደሮችን በአስር ሄክታር መሬት ላይ በዘር ብዜትና ማላመድ ስራ እንዲሳተፉ ማድረጉም ተገልጿል፡፡ በመስክ ጉብኝቱ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮችን ፣ ተመራማሪዎች አርሶአደሮችና የግብርና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም