በሰሜን ሸዋ 20 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ የተገነቡ ትምህርት ቤቶች ለአገልግሎት ተዘጋጁ

68
መስከረም 10/2012 በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን 20 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ ግንባታቸው የተጠናቀቀ ሶስት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለአገልግሎት መዘጋጀታቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ። በዞኑ በተያዘው ትምህርት ዘመን እድሜያቸው በትምህርት የደረሰ 69 ሺህ የሚበልጡ ህጻናት ተመዝግበዋል። የመምሪያው ኃላፊ አቶ ዓይነኩሉ አበበ ለኢዜአ እንደገለጹት በተያዘው የትምህርት ዘመን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ ግንባታቸው የተጠናቀቁ ሶስት ትምህርት ቤቶች ለአገልግሎት ዝግጁ ተደርገዋል ። ትምህርት ቤቶቹ የተገነቡት በሲያደብርና ዋዩ፣በእንሳሮና በመንዝ ወረዳዎች ነው። በተጨማሪም የ12 ትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻልና ለመማር ማስተማር ምቹ የማድረግ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል ። እንደ ኃላፊው ገለጻ ትምህርት ቤቶቹ ለመማር ማስተማር የሚያግዙ ቁሳቁሶች በክልሉ መንግስትና በዞኑ በኩል እንዲሟሉ እየተደረገ ነው። ትምህርት ቤቶችን ለመገንባትና ለማደራጀት ህብረተሰቡ 18 ሚሊዮን ብር የሚገመት የጥሬ ገንዘብ፣ የቁሳቁስና የጉልበት ተሳትፎ ማድረጉንም ጠቅሰዋል ። በአንጎለላ ጠራ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ደምሴ ፋንቱ በአካባቢያቸው የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ለማጠናከር በገንዘብና በጉልበት ማገዛቸውን ተናግረዋል። እድሜያቸው የደረሰ ህጻናት በወቅቱ እንዲመዘገቡ ቅስቀሳ በማድረግ መሳተፋቸውን ጠቀሰዋል ። በተያዘው ዓመት የተሻለ ወጤት ለማምጣት የክረምት የእረፍት ጊዜውን በንባብ ማሳለፉንና በወቅቱ መመዝገቡን የገለፀው ደግሞ በወረዳው ጽጌረዳ ቀበሌ ህዳሴ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ገብሩ ደምሴ ነው። በዞኑ በተያዘው ትምህርት ዘመን 1ሺህ 76 የአንደኛ፣ 64 የሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ተቀብለው እንደሚያስተምሩ ታውቋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም