የኦሮሚያ ክልል በ2010/11 የምርት ዘመን 203 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት አቅዷል

146
አዲስ አበባ ሰኔ 8/2010 በኦሮሚያ ክልል በ2010/11 የምርት ዘመን 203 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ገለጸ። የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሐምዛ መሐመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ዕቅዱን ለማሳካት የሚያስችል የግብዓት እየቀረበና ስልጠናም እየተሰጠ ነው። በምርት ዘመኑ ከ6 ሚሊዮን 60 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን የማሳ ዝግጅት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው 4 ነጥብ8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ እቅድ ተይዞ እስካሁን 3 ነጥብ6 ሚሊዮን ማዳበሪያ መቅረቡን ገልጸዋል። በምርት ዘመኑ ለማግኘት የታቀደው የምርት መጠን ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር የ52 ሚሊዮን ኩንታል ጭማሪ እንደሚኖረውም ተናግረዋል። የቀጣዩን የምርት ዘመን ለማሳደግ በሄክታር የሚገኘውን ምርት በአማካኝ ወደ 34 በመቶ ለማሳደግ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ቅድመ ዝግጅት እየተካሄደ መሆኑን አቶ ሐምዛ ጠቁመዋል። እስከአሁን ባለው ሂደት 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተለያዩ ተሸፍኗል። አርሶ አደሩ ሙሉ ፓኬጅ በመተግበር ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ እንዲጠቀም፣ በመስመር እንዲዘራ፣ በወቅቱ እንዲያርምና አስፈላጊ የተባይ መከላከያ ኬሚካሎች እንዲጠቀም በማድረግ ምርቱን ለመጨመር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። እቅዱን ለማሳካት አርሶ አደሩ የተለያዩ ፓኬጆችን በመተግበርና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የበለጠ እንዲሰራ ተደርጓል። የአርሶ አደሩን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ለማሻሻል ሙሉ ፓኬጅ ተጠቅሞ ከመስራት አንጻር ክፍተቶች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ሐምዛ ለአርሶ አደሩና ለባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት ችግሩን ለመፍታት እየተሞከረ እንደሆነ ገልፀዋል። በስልጠናው የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ምርትና ምርታማነትን ማሻሻያዎች ላይ አመራሮችንና አርሶ አደሮችን ጨምሮ  ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ስልጠና መሰጠቱን ጠቁመዋል። ስልጠናው የአመለካከትና የክህሎት ለውጥ የሚያመጣ በመሆኑ ዕቅዱን ማሳካት እንደሚቻል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው የምርጥ ዘርና የሌሎች ግብዓቶች አቅርቦት ካለፈው ዓመት አንጻር ሲታይ የተሻለ እንደሆነ ተናግረዋል። አሁን በክልሉ ያለው ሰላም የተረጋጋ በመሆኑ ለአርሶ አደሩ የግብዓት አቅርቦትን ለማድረስ የተመቻቸ ሁኔታ በመፍጠሩ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የሚያግዝ ምቹ ሁኔታ መሆኑን ምክትል ቢሮ ኃላፊው ጠቁመዋል። አርሶ አደሩ አንድ አካባቢ ላይ የሚመረቱ ተመሳሳይ ምርቶችን በኩታ ገጠም የማምረት ዘዴ በመጠቀም፣ መሬቱን ደጋግሞ በማረስ ምርት ለማሳደግ በሚያስችል ሰብል አይነት እንዲሸፍን እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል። በክልሉ ባለፈው የ2009/10 ምርት ዘመን ከ151 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም