ከጥንቃቄ ጉድለት ትናንሽ አጥቢ እንስሳት በአፍሪካዊያን ጤና ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑ ተገለጸ

84
መስከረም 10/2012 አፍሪካ በትናንሽ አጥቢ እንስሳት አያያዝ ጉድለት ምክንያት በህዝቦቿ ጤና፣ንብረትና ሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳትን እያስተናገደች መሆኑን ተገለጸ። በመቐለ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የነበረውን 13ኛ የአፍሪካ የትናንሽ አጥቢ እንስሳት ዓለም አቀፍ ሲምፖዚየም ትላንት ተጠናቀቀ ። በመድረኩ "የአይጦች አያያዝና ውጤቱ በአፍሪካ" በሚል ርዕስ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት በእንግሊዝ በግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮ ሳይንስ ኢንስቲቲዩት የኢኮሎጂ ፕሮፌሰር ስቲቨን በልማይን /StevenBelmain/ እንዳሉት አይጦች ከሰብል ጉዳት ባለፈ በሰዎች ጤና ላይም ችግር ያስከትላሉ። ከሰው ወደ ሰው በሚያስተላልፉት በሽታ በተለይም ህጸናትና እናቶች ጤና ላይ የከፋ ችግር እንደሚያስከትሉ ጠቁመው በምርምር የተገኙ የመከላከል ዘዴዎችን ተግባራዊ ማድረግ አዋጭ መሆኑንም አስረድተዋል። ሲምፖዚየሙም መሰል ችግሮችን በጋራ ለመፍታትና የምርምር ውጤቶችን ለመረዳት ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ አስረድተዋል። በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ተመራማሪና የዝግጅቱ አስተባባሪ ዶክተር ምህረቱ ዮናስ በበኩላቸው አይጦች በሰብል ላይ የሚያደርሱትን ጉዳትና የመከላከያ ዘዴ በሲምፖዚየሙ ትኩረት ያገኘ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል። በሰብል ላይ ከቡቃያው ጀምሮ እስከ ጎተራ ድረስ ከፍተኛ ውድመት የሚያደርሱ መሆናቸው ገልጸው በኢትዮጵያ 20 አዳዲስ ትናንሽ አጥቢ እንስሳት መገኘታቸውን በሲምፖዚየሙ ይፋ መደረጉን አስታውቀዋል። ቀደም ሲል የነበረው 80 የትናንሽ አጥቢ እንስሳት ዝርያ ቁጥርም አሁን ላይ 100 በመድረሱ ከአፍሪካ ደቡብ አፍሪካና ዲሞክራቲክ ኮንጎን አስከትላ ቀዳሚ መሆንዋን መረጋገጡን ዶክተር ደሳለኝ ገልጸዋል። ከቀረቡት ጥናቶች መካከል ትናንሽ አጥቢ እንስሳት በቫይረስ ተሸካሚነት ጉዳት የሚያደርሱበት እድል ከፍተኛ መሆኑንና ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግም በሲምፖዚየሙ ላይ መገለጹንና ከ40 አመታት በፊት የተሰሩ ጥናቶች በአዳዲስ ጥናቶች መከለሳቸውንም አስረድተዋል። የከተሞች መስፋፋትን ተከትሎ ቆሻሻ በአግባቡ ባለማስወገድ እየተበራከቱ የመጡ አይጦች በነዋሪዎች ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት ሌላው ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበ ጥናት እንደሆነም ዶክተር ምህረቱ ተናግረዋል። ሲምፖዚየሙ በአፍሪካ ትናንሽ አጥቢ እስሳት የሚታየውን የአጠባበቅ ጉድለት ለመቅረፍ ትልቅ ሚና አለው ያሉት ደግሞ በዘርፉ 30 አመት ጥናት ያካሄዱት በታንዛኒያ ሶኮይኔ ግብርና ምርምር ዩኒቨርሲቲ /sokoine univeresity of Agriculture / ተመራማሪ ፕሮፌሰር ርሆደስ ማኩንዲ /Rehodes makundi/ናቸው። "በትናንሽ አጥቢ እንስሳት የሚመጡ በሽታዎችን ከመከላከል ባለፈ ሲምፖዚየሙ አፍሪካውያን ተመራማሪዎች የአፍሪካ እድገት በምርምርና ጥናት ላይ እንዲመሰረትና በጋራ እንዲሰሩ የጎላ ፋይዳ አለው" ብለዋል። "ኢትዮጵያ ያሏትን ትናንሽ አጥቢ እንስሳት ለመጠበቅ የሚያስችል ሲፖዚየም ነው"ያሉት ደግሞ ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የመጡ ተሳታፊ ዶክተር ደሳለኝ እጅጉ ናቸው ። በአለማችን አሉ ከሚባሉ ትናንሽ አጥቢ እንስሳት ተማራማሪዎች ልምድ መቅሰም ለአገሪቱ ብዝሃህይወት ጥበቃ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ዶክተር ደሳለኝ ተናግረዋል። ትናንሽ አጥቢ እንስሳት በሰዎች ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት በምርምር አስደግፎ ለመከላከል የሚያስችል ተሞክሮ መቅሰማቸውን ዶክተር ደሳለኝ ተናግረዋል።። ከ25 ሀገራት የተውጣጡ ተመራማሪዎች ከ100 በላይ በአፍሪካ ትናንሽ አጥቢ እንስሳት ላይ ትኩረት ያደረጉ ጥናታዊ ፅሁፎች አቅርበዋል። ቀጣይ 14ኛው የአፍሪካ የትናንሽ አጥቢ እንስሳት ሲምፖዚየም በናሚቢያ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ናሚቢያ ላይ እንደሚካሄድ ታውቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም