በትግራይ ክልል ለሚገኙ 10 ታጋይ የጦር ጉዳተኞች ዘመናዊ ዊልቸር ድጋፍ ተደረገላቸው

192
መቀሌ ሰኔ 8/2010 በትግራይ ክልል የሚገኙ 10 ታጋይ የጦር ጉዳተኞች 700 ሺህ ብር ግምት ያለው ዘመናዊ ዊልቸር ድጋፍ ትናንት ተደረገላቸው፡፡ አካል ጉዳተኞቹ ባለሞተር ዌልቼር ድጋፍ ያገኙት ከማእገር ሜታል ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ባለቤት ከአቶ አብደልዓሊም ሙሳ ነው። አቶ አብደልዓሊም ሙሳ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በአገሪቱ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ለማስፈን ሲታገሉ አካላቸውን ያጡ የጦር አካል ጉዳተኞች አሁን ላገኙት ስራና ሀብት መሠረት መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ በቀጣይም አካል ጉዳተኞች በገንዘብና በቁሳቁስ ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ባለሃብቱ በመቀሌ ከተማ በ850 ሚሊዮን ብር ወጪ የሜታል ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ሁለተኛ ቅርጫፍ ለመክፈት ቦታ ተረክበው ወደ ስራ ለመግባት ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል። የትግራይ ክልል የታጋይ ጦር አካል ጉዳተኞች ማህበር ተወካይ አቶ ጨርቆስ ወልደማርያም እንዳሉት፣ ድጋፉ አካል ጉዳተኞች ከህብረተሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉና ወደ ስራ እንዲሰማሩ እንደሚያስችላቸው ገልፀዋል፡፡ለመቀላቀልና ወደ ስራ ለመግባት ከሁለት ሳምንት በፊትም አቶ ባህረ ገዛኸኝና ባለቤታቸው ከ600 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው 10 ተመሳሳይ ባለሞተር ዌልቼር ለአካል ጉዳተኞች ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡ በክልሉ አሁንም ባለሞተር ዌልቼር የሚያስፈልጋቸው ከ60 የሚበልጡ ታጋይ የጦር አካል ጉዳተኞች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ ድጋፍ ከተደረገላቸው አካል ጉዳተኞች መካከል ታጋይ ደስታ መብራህቱ እንዳሉት በአካላ ድጋፍ እጦት ቀደም ሲል ቤት ውስጥ በመዋል ጊዜያቸው ያሳልፉ እንደነበር ገልጸዋል። ከአሁን በኋላ ግን ያገኙትን ባለሞተር ዌልቸር በመጠቀም ወደ ስራ ለመሰማራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። ተመሳሳይ ድጋፍ የተደረገላቸው ታጋይ አሳየኸኝ ነጋሽ በበኩላቸው ከአሁን በፊት ዘመናዊ ያልሆነ የአካል ድጋፍ ይጠቀሙ ስለነበር ለ20 ዓመታት ከመኖሪያ ቤታቸው ግቢ ርቀው ለመውጣት ይቸገሩ እንደነበር ገልፀዋል፡፡ አሁን ባገኙት ዘመናዊ ዊልቼር በመታገዝ በሸቀጣ ሸቀጥ ስራ ለተሰማሩት ባለቤታቸው ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም