በሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ የተጣለው የኪሎ ሜትር ገደብ ለተወሰነ ጊዜ ተነሳ

72
መስከረም 10/2012 በሕዝብ መመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ የተጣለው የኪሎ ሜትር ገደብ ከዛሬ መስከረም 10 ቀን 2012 ዓም ጀምሮ ለአጭር ጊዜ መነሳቱን የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታወቀ። ገደቡ የተነሳው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ወደየተመደቡባቸው ዩኒቨርሲቲዎች በሚያደርጉት ጉዞ የትራንስፖርት እጥረት እንዳይገጥማቸው ለማድረግ ነው ተብሏል። በአገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መስፋፋት ጋር ተያይዞ በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች በአገሪቱ በሚገኙ 50 ያህል የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ናቸው። ወቅቱ እነዚህ በሁሉም የአገሪቱ አቅጣጫዎች በሚገኙት ዩኒቨርስቲዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ያሉት ተማሪዎች የእረፍት ጊዜያቸውን አጠናቀው ወደዩኒቨርሲቲዎቻቸው የሚገቡበት ነው። ገደቡ የተነሳውም ከዚህ ጋር በተያያዘ ተማሪዎች የትራንስፖርት እጥረት እንዳይገጥማቸው በማሰብ መሆኑን ባለስልጣኑ ዛሬ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል። በመሆኑም እርምጃው የትራንስፖርት አቅርቦቱን ለማሻሻልና የተማሪዎችን እንግልት ለመቀነስ ያግዛል ብሏል። ባለስልጣኑ ባወጣው መግለጫ መሰረትም ተሽከርካሪዎቹ  የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ለማጓጓዝ ብቻ ከመስከረም 10 አስከ ጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓም ድረስ ብቻ በኪሎ ሜትር ሳይገደቡ አገልግሎት መስጠት ይችላሉ። ለዚህም የክልልና የከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ተቋማት በመናኸሪያዎች ሰራተኞችን እንዲመደቡና ሒደቱን እንዲቆጣጠሩ ባለስልጣኑ አሳስቧል። የተቋማቱ ሰራተኞት ተሽከርካሪዎችን በመመደብና ተማሪዎችን ሳያቆራርጡ በቀጥታ ወደየ ዩኒቨርሲቲዎቹ የሚደርሱበትን ትራንስፖርት አገልግሎት በማቀናጀት ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይኖርባቸዋል ብሏል። የሚመለከተው ተቆጣጣሪ አካልም ጉዳዩን አውቆ ትብብር እንዲያደርግ ባለስልጣኑ ጥሪውን አቅርቧል። እስካሁን በተሽካሪዎች ላይ የነበረው የኪሎ ሜትር ገደብ ለአነስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ 150 ኪሎ ሜትር ፣ ለመለስተኛ ከ150 እስከ 250 ኪሎ ሜትርና ለአገር አቋራጭ ደግሞ ከ250 ኪሎ ሜትር በላይ መሆኑ ይታወቃል። በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች በመንግስትና በግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም