ዋልያዎቹ የቻን ውድድር የማጣሪያ ጨዋታቸውን ነገ ከሩዋንዳ አቻቸው ጋር ያደርጋሉ

91
መስከረም 10/2012 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ አገራት የእግር ኳስ ውድድር /ቻን/ የ2ኛ ዙር የመጀመሪያ ማጣሪያ ጨዋታውን ነገ ከሩዋንዳ አቻው ጋር ያደርጋል። በካሜሮን አስተናጋጅነት በጥር 2012 ዓ.ም በሚካሄደውና በአገር ውስጥ ሊግ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት 6ኛው የአፍሪካ አገራት እግር ኳስ ውድድር /ቻን/ የሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ማጣሪያ ጨዋታዎች ዛሬ እና ነገ ይካሄዳሉ። በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሩዋንዳ አቻው ጋር ነገ ከቀኑ 10 ሠዓት በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ጨዋታውን ያደርጋል። በአሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የሚመሩት ዋልያዎቹ ከመስከረም 4 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ለጨዋታው ዝግጅት ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን የመጨረሻ ልምምዳቸውንም ዛሬ ያደርጋሉ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሐምሌ 2011 ዓ.ም ቻን የመጀመሪያው ዙር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የጅቡቲ አቻውን በድምር ውጤት 5 ለ 3 በሆነ ውጤት አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉ ይታወሳል። በ37 ዓመቱ ሩዋንዳዊ አሰልጣኝ ቪንሰንት ማሻሚ የሚመራው የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ከኢትዮጵያ አቻው ጋር ላለበት ጨዋታ 26 ተጫዋቾችን ጨምሮ 47 ልዑካንን ይዞ ከትናንት በስቲያ አዲስ አበባ መግባቱ ይታወሳል። ብሔራዊ ቡድኑ ትናንት ጨዋታው ወደሚካሄድበት መቐለ ከተማ ሲገባ የትግራይ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ተወካይ አቶ ካህሳይ ፍስሀ አቀባበል አድርገውላቸዋል። በተጨማሪም ብሔራዊ ቡድኑ ትናንት ከቀኑ 10 ሠዓት ላይ የመጀመሪያ ልምምዱን በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ማድረጉን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለከታል። ጨዋታውን የሚመሩት ዳኞች ከኬንያ፣ ኮሚሽነሩ ከሱዳን እንደሆኑም ታውቋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱና የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ቪንሰንት ማሻሚ ጨዋታውን አስመልክቶ ዛሬ ከቀኑ በ11 ሠዓት በመቐለ አክሱም ሆቴል የቅድመ ጨዋታ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣሉ። ዋልያዎቹ በደርሶ መልስ ውጤት የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድንን ካሸነፉ ካሜሮን በምታስተናግደው የቻን ውድድር  መሳተፋቸውን ያረጋግጣሉ። በካሜሮን ለሚካሄደው ውድድር በሰሜን ዞን፣ በምዕራብ ዞን ኤ፣ በምዕራብ ዞን ቢ፣ በማዕከላዊ ዞን፣ ማዕከላዊ ምስራቅ ዞን እና ደቡብ ዞን ተከፋፍሎ ከሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ ማጣሪያ እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል። በሁለተኛው ዙር የሚካሄዱ የማጣሪያ ጨዋታዎች የደርሶ መልስ ውጤት አሸናፊ የሚሆኑ 15 ብሔራዊ ቡድኖች በቻን ውድድር ይሳተፋሉ። በሌላ በኩል በዩጋንዳ ዛሬ በሚጀመረው 12ኛው የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ /ሴካፋ/ ከ20 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ትናንት ውድድሩ ወደሚካሄድበት ስፍራ አቅንቷል። 20 ተጫዋቾችን ጨምሮ 26 ልዑካን ወደ ስፍራው ማቅናታቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። 11 ብሔራዊ ቡድኖች በሚሳተፉበት ውድድር በአስልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ የሚሰለጥነው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በምድብ ሁለት ከታንዛንያ፣ ዛንዚባርና ኬንያ ጋር ተደልድሏል። ቡድኑ ከነሐሴ 27 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ አዳማ ላይ ዝግጅቱን አድርጓል። ብሔራዊ ቡድኑ የመጀመሪያ ጨዋታውን ነገ በጂንጃ ከተማ በሚገኘው ካኪንዱ ስታዲየም ከቀኑ በ10 ሠዓት ከታንዛንያ አቻው ጋር ያደርጋል። የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ዛሬ ሲጀመር በጉሉ ከተማ በሚገኘው ፔስ ዋር ሚሞሪያል ስታዲየም በምድብ አንድ ሱዳን ከጅቡቲ ከቀኑ በ8 ሠዓት አዘጋጅ አገር ዩጋንዳ ከኤርትራ ከቀኑ 10 ሠዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በምድብ ሶስት ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያና ብሩንዲ ይገኛሉ። ኢትዮጵያዊያኑ ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ በመሐል ዳኝነት፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ በላቸው ይታየው በውድድሩ ላይ የሚያጫውቱ ይሆናል። የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ውድድር እስከ መስከረም 24 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ይቆያል። በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት /ሴካፋ/ የሚዘጋጀው ከ20 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው እ.አ.አ በ1971 በታንዛንያ አዘጋጅነት ነበር። ውድድሩ በሴካፋ አማካኝነት በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት ሴካፋ ባለበት የፋይናንስ ችግር ምክንያት ውድድሮችን ሳያካሂድ ቀርቷል። ለመጨረሻ ጊዜ የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር የተካሄደው እ.አ.አ በ2010 በዩጋንዳ አስተናጋጅነት ሲሆን ዩጋንዳ ኤርትራን አሸንፋ የዋንጫው ባለቤት መሆን ችላለች። የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር /ፊፋ/ ለሴካፋ ውድድሩን እንዲያዘጋጅ ባደረገው የ500 ሺህ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ አማካኝነት ውድድሩ ከዘጠኝ ዓመት መቋረጥ በኋላ ዛሬ የሚጀምር ይሆናል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም