የህገ- መንግስቱ ሩብ ምዕተ ዓመትና የብሄር ብሄረሰቦች በዓል በአዲስ አበባ ይከበራል

101
አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 10/2012 የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት የጸደቀበት ሩብ ምዕተ ዓመትና 14ኛው የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ቀደም ካሉት ዓመታት በተለየ ሁኔታ የሚከበር መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ። የዘንድሮው የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ ይከበራል ተብሏል። የበዓሉ አከባበር ዓብይ ኮሚቴ ያለፈው ዓመትን የስራ አፈጻፀምና በዘንድሮው ዝግጅት እቅድ ላይ ዛሬ ተወያይቷል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂምና የክልልና የከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች አፈ-ጉባኤዎች እንዲሁም የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንና መንግስታዊ ተቋማት ተወካዮች በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል። አፈ-ጉባኤዋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ቀኑ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የራሳቸውን ባህል ከማስተዋወቅ ባሻገር የሌሎችን ለማወቅ የሚያስችላቸውና የእርስ በእርስ መስተጋብራቸውን የሚያጠናክርላቸው ነው። የዘንድሮውን የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዓል ከሌላው ጊዜ የሚለየው ህገ-መንግስቱ ከፀደቀ ሩብ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረበት መሆኑ ነው ብለዋል። ከዚህም ሌላ ሁሉም ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን የተለማመዱበትና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ የመጡበት መሆኑም የዘንድሮውን የብሄር ብሄረሰቦች ቀን የተለየ ያደርገዋል ሲሉም ገልፀዋል። "ብዝሃነት የስጋት ምንጭ ሳይሆን የአንድነታችንና የአብሮነታችን መገለጫ በመሆኑ በዓሉ በአሁን ወቅት የሚስተዋለውን የብሄር ጥላቻ በሚፈታ መልኩ እንዲከበር ይደረጋል" ሲሉም አፈ-ጉባኤዋ ተናግረዋል። ''ህገ-መንግስቱ በሁሉም ዘንድ ሲከበር የአገሪቷን ሰላም ወደ ነበረበት መመለስ ይቻላል'' ያሉት አፈ-ጉባኤዋ አሁን በአገሪቷ እየታየ ያለው የብሄር ግጭት ከአመለካከት ችግር የመነጨ መሆኑን አስረድተዋል። የባለፉት 11 ዓመታት የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዓላት አከባበር ላይ ጥናት ተደርጎ ጥንካሬዎችና ክፍተቶች መለየታቸውን ያመለከቱት አፈ-ጉባኤዋ በቀጣይም ቀኑ የህዝቦች የእርስ በእርስ ግንኙነትን በሚያጠናክር መልኩ እንዲከበር በየደረጃው ያሉ አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት። የብሄር ብሄረሰቦችን እኩልነትና አንድነት ለማጠናከር እንዲቻል የዜጎችን አመለካከት የተሻለ ለማድረግ በሚያስችል መንገድ ነው የዘንድሮው በዓል የሚከበረው ተብሏል። ከዚህም ሌላ የዘንድሮው በዓል በተቻለ መጠን ወጪ ቆጣቢ እንዲሆን እንደሚደረግም ተመልክቷል። ለክብረ በዓሉም ''ህገ-መንግስታዊነት ለሰላምና ለአገራዊ አንድነት''፣''የህግ የበላይነት ለዘላቂ ሰላምና አገራዊ አንድነት'' እንዲሁም ''ህገ-መንግስታዊ ቃልኪዳናችን ለሰላማችን'' የሚሉ መሪ ሀሳቦች  በአማራጭነት ቀርበዋል። ኮሚቴው በተለይ ሶስተኛው መሪ ሀሳብ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግና በእርሱ እንዲፀና ምክረ-ሀሳብ ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ህገ-መንግስቱ ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ ም መጽደቁን ተከትሎ ከ1999 ዓ ም ጀምሮ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች አስተናጋጅነት  እየተከበረ ይገኛል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም