የግሸን ደብረ ከርቤ ንግስ በዓል ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

57
ደሴ ኢዜአ መስከረም9/2012 መስከረም 21 በሚከበረው ግሸን ደብረ ከርቤ ንግስ በዓል ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ ቅደመ ዝግጅት መደረጉን የደቡብ ወሎ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ገለጸ። የመምሪያው ኃለፊ አቶ ሱለይማን እሸቱ እንዳሉ በዞኑ አምባሰል ወረዳ በየዓመቱ መስከረም 21 በሚከበረው የንግስ በዓሉ ለመታደም ከውጭና ከሀገር ውስጥ በርካታ እንግዶች እንደሚመጡ ይጠበቃል። በበዓሉ ወቅት ስርቆትና ንግድ ቤቶች የተጋነነ ዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር እንዲሁም ተላላፊ በሽታዎች፤ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ጥበት፤ የውሃና የመብራት ችግሮች እንዳይከሰቱ ቅደመ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ እንግዶች ያለ ስጋት የመጣበትን ዓላማ እንዲያሳኩ ከዞን እስከ ወረዳ ኮሚቴ ተቋቁሞ መሰረተ ልማቶችን ከወዲሁ በማስተካከል ምቹ አድርጓል፡፡ ከዚህ ቀደም እንግዶች ወደ ቦታው በአንድ አቅጣጫ ብቻ ይገቡ እንደነበር ያመለከቱት ኃላፊው ተጨማሪ ሌላ መንገድ ከውጫሌ ግሸን ማሪያም በ220 ሚሊዮን ብር ተሰርቶ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ ከክልሉ መንግስት ጋር በመተባበር የውሃ ማጠራቀሚያ ጋኖች ፣ አዲስ የመብራት ትራንስፎርመር፤ የምግብ አዳራሽ፤ መጸዳጃ ቤቶች ፤ የንግድ ቦታዎችና የህክምና መስጫ ማዕከል ተመቻችቷል። በዓሉ ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ ለአለም እንዲተዋወቅ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው የወሎ ባህላዊ ምግቦች፤ አልባሳትና ሌሎች ባህላዊ መገለጫዎችም ለእንግዶች ለማቅረብ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን አብራርተዋል፡፡ የዞኑ ጸጥታና አስተዳደር መምሪያ ምክትል ኃላፊ ኮማንደር ጌታወይ ዘገየ በበኩላቸዉ “በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የጸጥታ ኃይሉ በየደረጃው ወደ ሥራ ገብቷል “ብለዋል፡፡ አሽከርካሪዎች ከታሪፍ በላይ እንዳያስከፍሉ፤ ወንጀሎች እንዳይፈጸሙና የተኝከርካሪ አደጋም እንዳይከሰት ከሰሜን ወሎ፤ ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደርና ሰሜን ሸዋ ዞኖች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል። ህገ ወጥ ተግባራት ሲፈጸሙ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ጊዜያዊ ፖሊስ ጣቢያዎችና የችሎት ቦታዎች መመቻቸታቸውን አመልክተዋልል፡፡ “በዓሉ ኃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ በሰላም እንዲከበር ከመስከረም 3 ጀምሮ አስፈላጊውን ቅደም ዝግጅት እያደረገን ነው “ ያሉት ደግሞ የግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማሪያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ አባ ለይኩን ወንድይፍራ ናቸዉ፡፡ ኢትዮጵያዊያንን የሚያገናኝ በመሆኑ ሀገራዊ አንድነት፤ ሰላም፤ ፍቅር፤ መቻቻልና አብሮነትን ለማጠናከር ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡   መስከረም 21 በሚከበረው የግሸን ደብረ ከርቤ ንግስ ዓዓል ከውጭና ከሀገር ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የእምነቱ ተከታዮችና ጎብኚ የሆኑ እንግዶች እንደሚመጡ ይጠበቃል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም