በግንባታ ጥራትና አፈጻጸም ላይ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ሊተገበር ነው

69
አዲስ አበባ መስከረም 9/2012  የግንባታዎች ጥራትና አፈጻጸም ላይ ጉልህ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ለመተግበር በዝግጅት ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት አስታወቀ። ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ሁለት የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ በተካሄደ ሙከራ ጥራትን በማሻሻል፣ የባለ ድርሻ አካላትን ቅንጅት በማጠናከርና በሌሎችም ለውጦች ተገኝተዋል ተብሏል። ኢንስቲትዩቱ ‘አውቶ ዴስክ’ ከተሰኘ የአሜሪካ ሶፍትዌር አምራች ድርጅት ጋር በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮንስትራክሽን ዘርፍ በሚሰራባቸው የሶፍትዌር ቴክኖሎጂዎች ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ አካሂዷል። የኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተር አቶ አስመሮም ታደሰ እንደተናገሩት ግንባታዎችን በጥራት፣ በጊዜና ወጪን በቆጠበ መልኩ ማከናወን የሚያስችል የህንጻ መረጃ ሞዴል ሶፍትዌር ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው። የቴክኖሎጂው ሶፍትዌርና አስፈላጊ መሳሪያዎች ግዢ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ መፈጸሙን ተናግረዋል። የፕሮጀክት አስተዳደር ብቃት አነስተኛ መሆን፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ያለመጠቀም፣ የጥራት መጓደልና ሌሎችም ከኮንስትራክሽን ዘርፉ ዋነኛ ችግሮች መካከል ጠቅሰዋል። የግንባታ ወጪዎች ከተመደበው በጀት ጋር ያላቸው ልዩነት ከፍተኛ መሆን፣ የባለ ድርሻ አካላት ቅንጅት ማነስ፣ በግንባታ ወቅት ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን አስቀድሞ አለመለየትና መፍትሄዎችን ያለማዘጋጀት፣ የስራ ተቋራጮችና አማካሪዎች ብቃት ማነስንም እንዲሁ። በመሆኑም ከፕሮጀክቶች ዲዛይንና እቅድ አወጣጥ እስከ አፈጻጸም ባሉት ደረጃዎች ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ስራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል ብለዋል። የህንጻ መረጃ ሞዴል ሶፍትዌር ቴክኖሎጂው በኮንስትራክሽን ዘርፉ ያሉ በርካታ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያስችልም ነው የተናገሩት። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ሁለት የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ሙከራ የተደረገ ሲሆን በተያዘው ዓመት ሶስተኛ ፕሮጀክት ላይ ይተገበራል። በሙከራ ፕሮጀክቶቹም በግንባታ ወቅት ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን በመቀነስ፣ ጥራት በማሻሻል፣ የባለ ድርሻ አካላትን ቅንጅት በማጠናከሩ በኩል ለውጦች መገኘታቸውን ገልጸዋል። ስለ ቴክኖሎጂው አጠቃቀም ለ18 ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱን፣ በቀጣይም ከሶፍትዌር ፈጣሪው ድርጅት ጋር በመሆን ስልጠና እንደሚሰጥ ተናግረዋል። ቴክኖሎጂው በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ ሙሉ ለሙሉ በቅንጅት እንዲተገበር ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱንና በቅርቡ ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል። በአምስት ዓመት ውስጥ በዘርፉ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ያስችላልም ነው የተባለው። እንደ አቶ አስመሮም ገለጻ ቴክኖሎጂው ለኮንስትራክሽን ዘርፉ ተስማሚ፣ አዋጪና ከአገራዊው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጋር ተጣጥሞ ተግባራዊ የሚሆን ይሆናል። የአውቶ ዴስክ የሽያጭ ስፔሻሊስት ማኔጀር ሚስተር ኒል ብሩከር በበኩላቸው ቴክኖሎጂው በአገሪቱ በስፋት ተተግብሮ ውጤታማ እንዲሆን ከባለ ድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም