አካል ጉዳተኞች የቴክኖሎጂና መረጃ ተደራሽ መሆን እንዳልቻሉ ተገለጸ

57

አዳማ  መስከረም 9/2012፡- በሃገሪቱ የሚገኙ አካል ጉዳተኞች የቴክኖሎጂና መረጃ ተደራሽ መሆን እንዳልቻሉ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን ገለጸ።

በአካል ጉዳተኞች የመረጃና ቴክኖሎጂ ተደራሽነት ዙሪያ የሚመክር የሁለት ቀን መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ በዚህ ወቅት እንዳሉት መረጃና ቴክኖሎጂ የአካል ጉዳተኛውን ሕይወት ያቀልላል።

“ሆኖም ዓለም ወደ ቴክኖሎጂ እየሄደና ከቴክኖሎጂውም በርካታ ትሩፋቶች እያገኘች ባለበት ሁኔታ የሀገሪቱ አካል ጉዳተኞች ግን አገልግሎቱ ተደራሽ ሊሆንላቸው አልቻለም” ብለዋል።

በተለይ በመረጃ ተደራሽነት ረገድ ያለው ዋና ችግር በሚመለከታቸው አካላት ትኩረት አለማግኘት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአካል ጉዳተኛውን ጉዳይ ተጧሪ አድርጎ የመመልከት ሁኔታ መኖሩን አመልክተዋል።

“ትምህርት ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ አለመሆን ትልቁ ማነቆ ነው “ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ይህም በቴክኖሎጂ ለመጠቀም ደንቃራ እንደሆነ ተናግረዋል።

በሀገሪቱ በቅርቡ የተሻሻለው የትምህርት ፍኖተ ካርታ አካል ጉዳተኞችን ሙሉ ለሙሉ ያገለለ ስለነበር እድሜያቸው ለትምህርት ከደረሱ አካል ጉዳተኞች ውስጥ የትምህርት እድሉን ያገኙት 7 ነጥብ 8 በመቶ ብቻ እንደሆነም አውስተዋል።

በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ለማቃለል ፌዴሬሽኑ “ስለኛ ያለእኛ አትስሩ “በሚል መርህ ከመንግስትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአዳማው መድረክም የዚሁ እንቅስቃሴ አካል እንደሆነ አመልክተው በተለይ በመረጃና ቴክኖሎጂ ተደራሽነት ረገድ ያሉ ማነቆዎችን ማስተካካል በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ለመምከር ታስቦ መዘጋጀቱን አብራርተዋል።

በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ዳይሬክተር አቶ አሳልፈው አህመዲን በበኩላቸው በአካል ጉዳተኞች ላይ ያለውን የተዛባ አመለካከት በማስወገድ ተገቢ ስራ መስራት ከሁሉም አካል እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

“ ከሀገሪቱ ህዝብ ቁጥር ውስጥ 17 ነጥብ 6 በመቶ የሚሆኑት አካል ጉዳተኞች እንደሆኑ በጥናት በመረጋገጡ እነሱን ተደራሽ ያደረገ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል” ብለዋል።

በመድረኩ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣የህዝብ ግንኙነትና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።