ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ባህልና ወግ የአካባቢያቸውን ሰላም እንዲጠብቁ አትሌት ደራርቱ ጠየቀች

113
መስከረም 9/2012 አዲሱ አመት ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ባህልና ወግ የአካባቢያቸውን ሰላም የሚጠብቁበት እንዲሆን አትሌት ደራርቱ ቱሉ ጠየቀች። አትሌት ደራርቱ ከኢዜአ ጋር በነበራት ቆይታ የተጠናቀቀው 2011 ዓ.ም መልካም ሁነቶች የተከናወኑበት እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች የሰላም መደፍረስ የታየበት እንደነበር አውስታለች። ''በመሆኑም አዲሱ አመት እርስ በርስ የምንተባበርበትና ለሰላም በጋራ የምንሰራበት ሊሆን ይገባል'' ብላለች። ኢትዮጵያውያን ግጭትንም ሆነ ደስታን የሚያስተናግዱበት የራሳቸው ባህልና ወግ ያላቸው ህዝቦች በመሆናቸው ያንን ለሰላም ማስፈን እንዲጠቀሙ ጠይቃለች። አዲስ አመት ተማሪው በትምህርቱ፣ ሰራተኛው በስራው ሁሉም በተሰማራበት ውጤታማ እንዲሆን ሰላም ቀዳሚው መሆኑንም ታነሳለች። ኢትዮጵያ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘፎች የምታደርገው ሽግግር እንዲሳካና ሁሉም የሚመኛትን የበለጸገች አገር ለመፍጠር ለሰላም ዋጋ መሰጠት እንዳለበት አትሌት ደራርቱ አስገንዝባለች። እንደ አትሌት ደራርቱ ገለፃ፤ ሁሉም ከቤቱ ጀምሮ የጎረቤቱን፣ የአካባቢውን ከዛም አልፎ የአለምን ሰላም ለመጠበቅ ሃላፊነት አለበት። እንደ አንድ ዜጋ የአገሯ ሰላም እንደሚያሳስባት በመግለጽ፤ ''እድሜና ጾታ ሳንለይ ሁላችንም በመተበባር እንስራ'' ስትል ጥሪ አቅርባለች በአገሩ ጉዳይ ሁሉም ያገባኛል ይመለከተኛል ብሎ ከሰራ ለውጥ እንደሚመጣ እምነቷን ገልጻ፤ ''ይህ ካልሆነ ግን የምናጣው ቤተሰባችንና አገራችንን ነው'' ስትል በአጽንኦት ተናግራለች። "ኢትዮጵያውያን እንደ ቀደመው ባህላችን ተደማምጠንና ተቻችለን በልዩነታችን አብረን መኖር የምንችል ነን" ስትልም ሃሳቧን አጠናክራለች። በአዲሱ አመት ለአገራችን ሰላም ዘብ በመቆምና መልካሙን በማሰብ በአንድነት ችግሮችን ለመፍታት እንተባበር ብላለች። በአሮጌው አመት የነበረው የሰላም መደፍረስ ዳግም እንዳይመለስ በአዲሱ አመት እጅ ለእጅ በመያያዝ፣ በመነጋገርና በሰለጠነ መንገድ መፍታት እንደሚገባ አትሌት ደራርቱ መልዕክት አስተላልፋለች።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም