በኤሊደአር እና ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳዎች 29 የክላሽንኮቭ ጠመንጃዎችና ጥይት ሲያጓጉዙ የተገኙ ግለሰቦች ተያዙ

92
ሰመራ/ ጎንደር ኢዜአ መስከረም 9/2012፡- በአፋር ኤሊደአር እና በአማራ ክልል ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳዎች 29 የክላሽንኮቭ ጠመንጃዎችና 3ሺህ 666 ጥይት ሲያጓጉዙ የተገኙ ግለሰቦች መያዛቸው ተገለጸ። የኤሊደአር ወረዳ ፖሊስ ወንጀል መከላከል ኃላፊ አቶ ሁመድ መሃመድ እንደተናገሩት መስከረም 6 /2012ዓ.ም በወረዳው ማንዳ ቀበሌ ምሽት አምስት ሰዓት አከባቢ የታርጋ ቁጥሩ ኮድ3-50257 አ.አ የሆነ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ ላይ 29 ባለሰደፍ ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ተሸሽጎ ተገኝቷል። ጨለማን ተገን በማድረግ በተሽከርካሪው ሲጓጓዝ ከነበረው ጠመንጃ ጋር 25 ባዶ ካርታዎችም ተገኝተዋል። መሳሪያውን ወደ መሃል ሀገር ለማሳለፍ ታስቦ የተዘጋጀ አንደነበር ኃላፊው አመልክተው አሽከርካሪውና ረዳቱ  እንዲሁም ሌላም ተጠርጣሪን ጨምሮ ሰዎች ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን አስረድተዋል። በሌላ በኩል ደግሞ በአማራ ክልል አርማጭሆ ወረዳ 3ሺህ 666 ህገ-ወጥ ጥይት መገኘቱን የወረዳው አስተዳደር ፀጥታ ጽህፈት ቤት አስታወቋል፡፡ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ እሸቱ ስመኘው ለኢዜአ እንደገለጹት ጥይቱ የተገኘው  መነሻውን አብርሃጅራ ከተማ አድርጎ ወደ  ጠገዴ ወረዳ ሶሮቃ ከተማ በተሽከርካሪ ሲጓጓዝ ትናንት ነው። የታርጋ  ቁጥር ኮድ 3 -38628 አ.አ በሆነ አይሱዙ የጭነት ተሸከርካሪ ውስጥ ተደብቆ የተገኘው ጥይቱ  በወረዳው የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል ከፖሊስ፣ ከልዩ ኃይልና ሚሊሻ አካላት በሚደረግ የኬላ ቁጥጥር እንደሆነ አመልክተዋል። አሽከርካሪው ለጊዜው  ቢያመልጥም  ረዳቱ ተይዞ ምርመራ እየተደረገበት እንደሚገኝ ኃላፊው ተናግረዋል። በወረዳው ከዚህ ቀደም ከሁለት ወራት በፊት 908 ህገ-ወጥ ጥይትና ሁለት ክላሽንኮቭ መሳሪያ ከህብረተሰቡ በተደረገ ጥቆማ መያዙንም አስታውሰዋል፡፡ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርንና የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል ህብረተሰቡ ተሳትፎውን  እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል፡፡ ከሁለት ቀናት በፊት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ታች አርማጭሆ ወረዳ 3ሺ555 ህገ-ወጥ የብሬን ጥይት መያዙም ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም