ኢትዮጵያ የኒውክለር ቴክኖሎጂን ለተለያዩ የልማት ስራዎች መጠቀም የሚያስችላትን ተጨማሪ የፕሮቶኮል ስምምነት ተፈራረመች

89
መስከረም 9/2012 ኢትዮጵያ የኒውክለር ቴክኖሎጂን የኤሌክትሪክ ኃይልን ጨምሮ ለተለያዩ የልማት ስራዎች መጠቀም የሚያስችላትን ተጨማሪ የፕሮቶኮል ስምምነት ተፈራረመች። ኢትዮጵያ ስምምነቱን የፈረመችው ከኒኩሊየር ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከናወኑ ተግባራትን ከሚቆጣጠረው የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር ነው። “የተጨማሪ ፕሮቶኮል” ስምምነቱ አገሪቱ ከዚህ በፊት የፈረመቻቸውን ሌሎች ስምምነቶች ለማጠናከር በኤጀንሲው የወጣ ተጨማሪ የግልፀኝነት ግዴታዎችን የሚያስቀምጥ ነው። የኒውክሌር ቴክኖሊጂ የተለያዩ አካላት እጅ ላይ ሲገባ ሌሎችን ጉዳት ላይ ይጥላል የሚል ስጋት በመኖሩ ማንኛውም አገር ኒውክሌር ማበልጸግ የሚችለው ከዓለም አቀፉ የኒኩሊየር ኤጀንሲ ፈቃድ ሲያገኝ ነው። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር የሚዲያና ፕሬስ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ አለምነው ለኢዜአ እንዳሉት ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ጋር በሰላምና በመቻቻል አብሮ የመኖር የረጅም ጊዜ እሴት ያላት እንደመሆኗ ቀደም ሲል በስምምነት ማዕቀፉ ውስጥ ገብታ የኒውክለር ኃይልን ለልማት ለማዋል እየሰራች ትገኛለች። አገሪቱ ተጨማሪ የፈረመቻቸው የግልጽነት ስምምነቶችም በዘርፉ ልምድ ካላቸው አገሮች ድጋፍ እንንድታገኝ ያግዛታል ተብሏል። ስምምነቱ የኒኩሊየር ቴክኖሎጂን ለኤሌክትሪክ ኃይል፣ ለግብርና፣ ለጤና፣ ለኢንዱስትሪ  ዘርፎች በማዋል ልማቷን ታፋጥንበታለችም ብለዋል። ዓለምን ከኒውክሌር ስጋት ነጻ  ለማድረግ ኤጀንሲው የሚያወጣቸውን ህጎችና አሰራሮች ተግባራዊ እንዲሆኑ ኢትዮጵያም ጠንክራ የምትሰራ መሆኑን በስምምነቱ አረጋግጣለች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም