ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የቻን የማጣሪያ ጨዋታ የሚያደርገው የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ አዲስ አበባ ይገባል

80

አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 8/2012 ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የአፍሪካ አገሮች የእግር ኳስ ውድድር (ቻን) የማጣሪያ ጨዋታ የሚያደርገው የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ ይገባል።

ስድስተኛው የአፍሪካ አገሮች የእግር ኳስ ውድድር (ቻን) በጥር ወር 2012 ዓ.ም በካሜሮን አስተናጋጅነት ይካሄዳል።

በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ የሚደረጉ የሁለተኛና የመጨረሻ ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት የሚካሄድ ሲሆን እሁድ መስከረም 11 ቀን 2012 ዓ.ም በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰአት ኢትዮጵያና ሩዋንዳ የሚያደርጉት ጨዋታ ይገኝበታል።

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚጫወተው የርዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችና ሌሎች ልዑካንን ጨምሮ 47 ልዑካን ዛሬ ከምሽቱ ሁለት ሰአት አዲስ አበባ እንደሚደርሱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ባህሩ ጥላሁን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በ37 ዓመቱ ርዋንዳዊ አሰልጣኝ ቪንሰንት ማሻሚ የሚመራው ብሔራዊ ቡድን ነገ ጨዋታው ወደ ሚካሄድበት መቐለ ከተማ በማምራት ልምምድ ማድረግ እንደሚጀምርም ተናግረዋል።

ጨዋታውን የሚመሩት ዳኞች ከኬንያ የጨዋታው ኮሚሽነር ከሱዳን እንደሆኑም ጠቁመዋል።

በአሰልጣኝ ኢንስራክተር አብርሃም መብራቱ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከርዋንዳ አቻው ጋር ላለበት ጨዋታ መስከረም 3 ቀን 2012 ዓ.ም መቐለ ከተማ በመግባት ከመስከረም 4 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለጨዋታው ዝግጅት እያደረገ ይገኛል።

አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ለተጫዋቾች ባደረጉት ጥሪ መሰረት 24 ተጫዋቾች በብሔራዊ ቡድኑ ተካተው ልምምድ እያደረጉ እንደሆነም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም ቻን የመጀመሪያው ዙር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የጅቡቲ አቻውን በድምር ውጤት 5 ለ 3 በሆነ ውጤት አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉ ይታወሳል።

ዋልያዎቹ በደርሶ መልስ ውጤት የርዋንዳ ብሔራዊ ቡድንን ካሸነፉ ካሜሮን በምታስተናግደው የቻን ውድድር ላይ መሳተፋቸውን ያረጋግጣሉ።

በካሜሮን ለሚካሄደው ውድድር በሰሜን ዞን፣ በምዕራብ ዞን ኤ፣ በምዕራብ ዞን ቢ፣ በማዕከላዊ ዞን፣ ማዕከላዊ ምስራቅ ዞን እና ደቡብ ዞን ተከፋፍሎ ከሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል።

በሁለተኛው ዙር የሚካሄዱ የማጣሪያ ጨዋታዎች የደርሶ መልስ ውጤት አሸናፊ የሚሆኑ 15 ብሔራዊ ቡድኖች በቻን ውድድር ይሳተፋሉ።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ ስድስተኛው የአፍሪካ አገሮች የእግር ኳስ ውድድር (ቻን) ውድድር አስተናጋጅነት ከሁለት ዓመት በፊት ለኢትዮጵያ ሰጥቶ እንደነበር የሚታወስ ነው።

ያም ቢሆን መንግስት ለውድድሩ የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን ዝግጁ አለመሆኑን በመግለጽ ኢትዮጵያ ውድድሩን እንደማታስተናግድ በመግለጿ ካፍ የቻን ውድድር አስተናጋጅነትን ለካሜሮን መስጠቱ አይዘነጋም።

ኢትዮጵያ ውድድሩን እንደማታስተናግድ ከመግለጿ በፊት የካፍ የቁጥጥር ቡድን ባደረገው ግምግማ ኢትዮጵያ በሚፈለገው ፍጥነት ለውድድሩ የሚያስፈልገውን ቅድመ ዝግጅት እያደረገች አለመሆኑንም ገልጾ እንደበርም ይታወቃል።

የአፍሪካ አገሮች ዋንጫ (ቻን) በአገር ውስጥ ሊግ ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ብቻ የሚያሳትፍ የውድድር መድረክ ሲሆን በየሁለት ዓመት የሚካሄድ ነው።

በካሜሮን በሚካሄደው የቻን ውድድር 16 ብሔራዊ ቡድኖች ይሳተፋሉ።