ህብረተሰቡ ለሰላም ዘብ ሊቆም እንደሚገባ የኃይማኖት አባቶች አሳሰቡ

52
መቱ ኢዜአ መስከረም 8/2012 ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የዕድገት ደረጃ ለማድረስ ህብረተሰቡ ለሰላም ዘብ ሊቆም እንደሚገባ በኢሉአባቦር ዞን የኃይማኖት አባቶች አሳሰቡ:: ከዞኑ ወረዳዎች የተወጣጡ የተለያዩ የኃይማኖት ተቋማት አባቶች ዛሬ  በመቱ ከተማ የሰላም ውይይት አካሂደዋል:: በውይይቱ ወቅት  እንዳሉት የአሁኑ ትውልድ ዘመናትን የተሻገሩ የመከባበር ፣የመቻቻልና የመፋቀር ባህሉን ይበልጥ በማጎልበት ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት አለበት:: በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የኢሉአባቦር ሀገረ ስብከት ስራ አስከያጅ ሊቀ ትጉሀን ብርሀኑ መንገሻ ማንኛውም ልማት የሚረጋገጠው አስተማማኝ ሰላም ሲሰፍን መሆኑን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊረዳ እንደሚገባ አመልክተዋል:: " የኃይማኖት ተቋማት እርስ በእርስ በመደማመጥና በመደጋገፍ ተከታዮቻቸውን አርአያቸውን እንዲከተሉ መስራት ይጠበቅባቸዋል "ብለዋል:: ከአሌ ወረዳ የተሳተፉት ሼህ ካሚል ከማል በበኩላቸው በአንዳንድ አካባቢዎች ህብረተሰቡ መብቱን እንደሚጠይቀው ሁሉ ግዴታውን መወጣት እንደሚኖርበት ተናግረዋል። በኃይማኖት ተቋማት አካባቢ ከይዞታ ጥያቄ ጋር ተያይዞ የሚነሱት ግጭቶች ለአምልኮ ቤቶች ግንባታ ፈጣን ምላሽ ባለመሰጠቱ መሆኑን ጠቁመው  ተቋማቱ ለሚጠይቁት የቦታ ጥያቄ የሚመለከተው አካል በፍጥነት ምላሽ እንዲሰጥም አመልክተዋል:: "በአሁኑ ወቅት መንግስት የሚከተለው የፍቅር ፣የይቅርታና አንድነት መንገድ የሁሉም ኃይማኖቶች አስተምህሮት በመሆኑ ህብረተሰቡ ለተግባራዊነቱ ሊተጋ ይገባል "ያሉት ደግሞ ከዲዱ ወረዳ በውይይቱ የተሳተፉት ቄስ ደሳለኝ ደገፉ ናቸው:: ህብረተሰቡ የመቻቻል፣ የመደማመጥና መከባበር ባህሉን በማሳደግ ያደገች ሀገር ለመፍጠር ሊሰራ እንደሚገባ አስሳስበዋል:: የኢሉአባቦር ዞን አስተዳደርና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበራ ሽፈራው በበኩላቸው አስተማማኝ ሰላም እንዲረጋገጥና የተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ ፍሬ እንዲያፈራ የኃይማኖት አባቶች ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል:: ህብረተሰቡ በተለያዩ ጊዜያት የሚያቀርባቸው ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ ሊፈቱ እንደሚችሉ የኃይማኖት አባቶች ግንዛቤ ማስጨበጥ እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል:: ለአንድ ቀን  በተካሄደው ውይይት ከዞኑ 11 ወረዳዎች የተወጣጡ የተለያዩ ኃይማኖት ተቋማት መሪዎችና አባቶች ተካፍለዋል::
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም