በዓላት ለቱሪዝም እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው

112
መስከረም 8/2012 ባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓላት ለቱሪዝም እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የቱሪዝም ባለሙያዎች ገለጹ። በየዓመቱ የሚከበረው የአለም የቱሪዝም ቀንም የቱሪዝም ዘርፍ እንዲያድግ እና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር የላቀ አስተዋጽኦ  እያደረገ መሆኑን ባለሙያዎቹ ገልፀዋል። የአክሱም ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ገብረመድህን ፍጹም ብርሃነ እንዳሉት በአክሱም የህዳር ጽዮን፣ የሆሳእናና የአይነዋሪ ሀይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት በየአመቱ በድመቅት ይከበራሉ። በእነዚሁ በዓላት ላይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የአገር ውስጥ ጎብኚዎች  የሚገኝባቸው በዓላት ከመሆናቸው ባለፈ በዓላቱ አገራዊ አንድነትና ማህበራዊ ግንኙነት የሚያጠናክር መዳላድል እየፈጠሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ከበዓላቱ ውጭ በአክሱም የሚገኙ ጥንታዊ ቅርሶችን ለመጎብኘት የሚመጡ የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች በየአመቱ በአማካይ ስድስት ሺህ ጭማሪ እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል። በተጠናቀቀው 2011 በጀት አመትም ከ61ሺህ በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች ቅርሶቹን የጎበኙ ሲሆን፣ ከዘርፉ 150 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል። ሃላፊው አክለውም፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓላት ሲከበሩ የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር እና በዘርፉ የተሰማሩ ዜጎች ተጠቃሚነት በማሳደግና ገቢ በማያስገኘት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም የአለም የቱሪዝም ቀንን ምክንያት በማድረግ የአክሱም ከተማ ነዋሪዎች ይበልጥ በባለቤትነት ስሜት እንዲሰሩ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የአርኪዮሎጂና ቱሪዝም ኢንስቲዩቲት ዳይሬክተር አቶ ተክለብረሃን ለገሰ በበኩላቸው፣ ተቋማቸው የቱሪስት ፍሰቱን ለማሳደግ በሰው ሀይል ስልጠናና በጥናትና ምርምር ስራዎች ድጋፍ እያደረገ ነው። ዩኒቨርስቲው በየአመቱ ከ30 በላይ ባለሙያዎች በማሰመረቅ ያለውን የሰለጠነ ሰው ሃይል እጥረት በመቅረፍ የቱሪዝም ልማት እንዲያድግ ድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ማህበረሰብ ተኮር የቱሪዝም እድገት ተግባራዊ ለማድረግም ዩኒቨርሲቲው በክልሉ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር እየሰራ እንደሆነ ነው አቶ ተከለበረሃን የተናገሩት። በክልሉ የቱሪዝም ልማትን ለማሳደግ የአክሱምና መቀሌ ከተሞች፣ የገርዓልታ ሰንሰላታማ ተራሮችና የሓሸንገ ሃይቅና አካባቢው ሞዴል የቱሪስት መስህብ ተብለው ተለይተው ከአራቱ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ 36 ምሁራን በትብብር እየሰሩ መሆናቸውንም  ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ካላት የቱሪዝም ሃብት ተጠቃሚ እንድትሆን ሰላምና መረጋጋት ላይ ተኩረት በማድረግ ሊሰራ እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ የአክሱም አስጎበኚዎች ማህበር አስተባባሪ አቶ ጉዕሽ ፍስሃ ናቸው። ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘው ገቢ ለማሳደግ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር በመተባባር ሰላምን ለማስፈን የጋራ ጥረት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። የቱሪስት ማረፊያ ቦታዎች እና የትራንስፖት አገልግሎት አሰጠጣጥ  ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ማህበሩ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን አቶ ጉዕሽ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም