ኅብረተሰቡ ባለው አቅም የሀገር ባለውለታ የሆኑ አረጋውያንን እንዲደግፍ ጥሪ ቀረበ

96

መስከረም 8/ 2012 ኅብረተሰቡ መስዋዕትነት ከፍለው ሀገርን እዚህ ላደረሱ የእድሜ ባለፀጎች አክብሮትና ፍቅርን በመስጠት ማህበራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ።

ዓለም አቀፉ የአረጋውያን ቀን በኢትዮጵያ ለ28ኛ ጊዜ በዓለም ደግሞ ለ29ኛ ጊዜ መስከረም 20 ቀን 2012ዓ.ም ታስቦ ይውላል።

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለእነዚህ ባለውለታዎች ድጋፍ እንዲውል “የእድሜ ባለፀጎችን በማክበርና በመደገፍ እንመረቅ” በሚል መሪ ሃሳብ ሀገራዊ ንቅናቄ ጀምሯል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ አየለች እሸቴ ቀኑን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ንቅናቄው በሚኒስቴሩ አስተባባሪነትና በሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የሚካሄድ ነው።

የንቅናቄው መሪ ሃሳብ መከባበር፣ መደጋገፍ፣ ፍቅርን መስጠት፣ መተሳሰብንና መደማመጥንም የያዘ ነው ብለዋል።

ንቅናቄው የአረጋውያንን ጉዳይ በአንድ ቀን አስቦ ከማለፍ በተጨማሪ የመደጋገፍ ባህልን ለማጎልበት እንዲሁም የተሸረሸረውን የመከባበር እሴትን ወደ ነበረበት ለመመለስና ትውልዱን ለመቅረፅም አስተዋፅኦ ያደርጋል ነው ያሉት።

“አረጋውያን ያላቸውን የመከባበር ፀጋ ሊያስተላልፉልን ዝግጁ ናቸው” ያሉት ወይዘሮ አየለች፤ ኀብረተሰቡም የእነሱን አርአያ በመከተል አክብሮቱንና ፍቅሩን መግለፅ እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

ሀገሪቷን ጠብቀው ለትውልድ ያስተላለፉ የእድሜ ባለፀጎች አረጋውያን አሁንም ለሰላም መረጋገጥ፣ ለማህበራዊ እሴቶቻችን መጎልበት እንዲሁም ለኢኮኖሚ እድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆኑን በመግለፅ።

ንቅናቄው በኀብረተሰቡና በባለድርሻ አካላት  ግንዛቤን መፍጠር የሚያስችልም ነው ተብሏል።

አረጋውያንን መደገፍ ችሮታ ሳይሆን መብታቸውን የማክበርና ኃላፊነትን መወጣት መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባም ጠቁመው ንቅናቄው መልካም መስራትንና የበጎ ፍቃድ ስራን የምናስተምርበትም ነው ብለዋል።

ንቅናቄው እስከ መስከረም 20 ድረስ በተለያዩ ተግባራት የሚቀጥል መሆኑንም በመጠቆም።

በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ አረጋውያን እንዴት መደገፍ አለብን? የሚለውን መልዕክት ለማስተላለፍም መታቀዱንና ይህ ስራም ከጳጉሜ ጀምሮ እየተሰራበት ያለ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከአርቲስቶችና ከኪነጥበብ ባለሙያዎች ጋር በአረጋውያን ጉዳይ ላይ በተደረገው ውይይት ባለሙያዎቹ በጥበብ ስራዎቻቸው ለመደገፍ ቃል መግባታቸውንም ገልፀዋል።

ድጋፍና ፍቅርን ለሚሹ አረጋውያን የገቢ ማሰባሰቢያ ለማድረግ የታሰበ ሲሆን በጥሬ ገንዘብ ለመደገፍ ለሚፈልጉ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንት 1000295674745 መሆኑን አሳውቀዋል።

በቁሳቁስና አልባሳት ለመርዳት የሚፈልግም በፒያሳ፣ መገናኛ፣ ሜክሲኮ፣ መስቀል አደባባይና ካሳንቺስ በሚገኘው በሚኒስቴሩ ግቢ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች አማካኝነት ከዛሬ ጀምሮ መለገስ እንደሚችልና በክልሎችም የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩን እንደሚመሩ አስረድተዋል።

በሚገኘው ድጋፍም 10ሺህ ያህል አረጋውያንን ለመደገፍ መታቀዱን ተናግረዋል።

ለአረጋውያን የሚደረገው ድጋፍ በዘላቂነትና ህጋዊ ማዕቀፍ ኖሮት መቀጠል እንዲችልና ሁሉም ኀብረተሰብ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣም የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉም ብለዋል።

የኢትዮጵያ አረጋውያንና ጡረተኞች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ክፍሉ በበኩላቸው ወቅቱ አረጋውያንን አንድ ቀን ከማሰብ ባለፈ ክብር በመስጠት ወደ ተግባር የተገባበት ነው ብለዋል።

“አረጋውያንን መደገፍ ላደረጉት አስተዋፅኦ ትንሽ ጠብታ እንደማዋጣት ነው” ያሉት አቶ ጌታቸው፤ ኀብረተሰቡ የሀገር ባለውለታ የሆኑ አረጋውያንን በመደገፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል።

ከመስከረም 18 ቀን 2012ዓ.ም ጀምሮ ለሶሰት ቀናት በሚሊኒየም አዳራሽ አረጋውያን የሚመርቁበት፤ ህብረተሰቡ ደግሞ እግር በማጠብና ልብስ በማልበስ ያለውን ክብርና ፍቅርን የሚገልጹበት መርሃ ግብር ይከናወናል፡፡

በእነዚህ  ቀናት የጤናና የትራንስፖርት አገልግሎት በነፃ እንዲያገኙ የሚደረግ ሲሆን መስከረም 20 ቀን 2012ዓ.ም በማርሽ ባንድ የታጀበ የእግር ጉዞ ይኖራልም ተብሏል።

በሀገሪቱ አድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ ከ6 ሚሊዮን በላይ አረጋውያን መኖራቸውም ከሚኒስቴሩ  የተገኘው መረጃ ያመለክታል።