ባህርዳር ሞጣ ደጀን የአስፓልት መንገድ ግንባታ ምረቃ እየተካሄደ ይገኛል

228

መስከረም 8/2012 ከባህር ዳር – ሞጣ – ደጀን የተገነባው 175 ኪሎ ሜትር የኮንክሪት አስፓልት መንገድ ግንባታ የኢፌድሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት ምረቃ እየተካሄደ ነው።

በአሁኑ ወቅትም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎች የክልልና የፌደራል ከፍተኛ አመራሮች በአሁኑ ወቅት መንገዱን በመጎብኘት ላይ ናቸው፡፡

መንገዱ በኢትዮጰያ መንግስት ሙሉ ወጪ በሁለት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር የተገነባ መሆኑንም የፌደራል መንገዶች ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ተናግረዋል።

የመንገዱ መገንባትም የአካባቢውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ከማቃለሉ ባለፈ ባህር ዳር- ሞጣ – ደጀን ወደ አዲስ አበባ የሚደረገውን ጉዞ በ80 ኪሎ ሜትር ማሳጠር ያስቻለ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ደረጃውን ጠበቆ የተገነበው መንገዱ  በአካባበው በስፋት የሚመረተውን የግብርና ምርት ወደ ማዕከላዊ ገበያ በቀላሉ ለማጓጋዝና ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችን ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

መንገዱ የተገነባው በሁለት አለም አቀፍ የቻይና የመንገድ ስራ ድርጀቶች ሲሆን ግንባታው አምስት ዓመት መጨረሱን ተናግረዋል።

ከዚህ መንገድ ምረቃ ቀጥሎም ከባህር ዳር ጢስ አባይ የኮንክሪት አስፓልት መንገድ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥና የማስጀመር ስራ ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል።