ለዘንድሮው የኢሬቻ በዓል አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል

94
መስከረም 7/ 2012 ዘንድሮ በአዲስ አበባ እና ቢሾፍቱ ከተሞች ለሚከበረው የኢሬቻ በዓል አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ። መላው ኢትዮጵያዊያን የበዓሉ ታዳሚ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርቧል። የዘንድሮውን የኢሬቻ በዓል ዝግጅት አስመልክቶ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪም ዝቢሮ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። የቢሮው ኃላፊ አቶ ግርማ ኃይሉ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት የአዲስ አበባውን "የሆራ ፊንፊኔ" እና የቢሾፍቱውን "ኦራ አርሰዲ" ኢሬቻ በዓላትን ለማክበር የተካሄደው ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል። በዓሉ ባዛሮችን፣ የባህል ፌስቲቫሎችን፣ ሩጫንና የሙዚቃ ኮንሰርትን ጨምሮ በተለያዩ ሁነቶች ይከበራል። የ"ሆራ ፊንፊኔ" ኢሬቻ በዓል ከረጅም ዓመታት መቋረጥ በኋላ በአዲስ አበባ መከበሩና በመላው አገሪቱም አዲስ የለውጥ ሂደት መጀመሩ የዘንድሮውን የኢሬቻ በዓል የተለየ ያደርገዋል ብለዋል። በዓሉ የኦሮሞ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያዊያን ህዝብ በመሆኑ ሁሉም በጋራ የሚያከብሩት በዓል ነው ሲሉም ተናግረዋል። የኢሬቻ በዓል ከገዳ ስርዓት የሚመነጭና ከሃይማኖትና ፖለቲካ አስተሳሰብ በፀዳ መንገድ መላው ህዝብ ሳይለያይ በጋራ የሚያከብረው በዓል መሆኑንም ገልጸዋል። ኢሬቻ የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት በዓል መሆኑን ጠቁመው ሁሉም በዓሉን በዚህ መንፈስ ያከብረው ዘንድ አሳስበዋል። የኢሬቻ በዓል ኢትዮጵያን ለውጭው ዓለም ለማስተዋወቅ የሚያግዝ የቱሪስት መስህብም ጭምር ነው ብለዋል። "የኢሬቻ በዓል ከመጠላላት ወደ መፋቀር ከመገፋፋት ወደ አንድነት እና እርቅ ለመሸጋገር ልንጠቀምበት እንችላለን" ሲሉም ገልጸዋል። የምስጋና ቀን የሆነው ኢሬቻ በዓል በተለያዩ የኦሮሚያ ክፍሎች በዓመት ሁለት ጊዜ ይከበራል። የመጀመሪያው የክረምት መውጣትን ተከትሎ በውሃማ አካባቢዎች የሚከበር ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በበልግ ወቅት በተራራማ አካባቢዎች ይከበራል። በዓሉ መስከረም 24 እና 25 ቀን 2012 ዓም በአዲስ አበባ እና በቢሾፍቱ ይከበራል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም