ኢትዮጵያ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ግድቡ የሚሞላበትን ምክረ ሀሳብ ይዛ ትቀርባለች- የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር

100
መስከረም 7/ 2012  ኢትዮጵያ በሶስትዮሹ ውይይት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ውሃ የሚሞላበትን ምክረ ሀሳብ እንደምታቀርብ የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አስታወቀ። በሚቀጥለው ዓመት ታህሳስ የግድቡ ሁለት ተርባይኖች ሃይል ማመንጨት እንደሚጀምሩም ተገልጿል። ባለፈው ዓመት መስከረም ወር በአዲስ አበባ ተካሂዶ ከነበረው የኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳነ የሶስትዮሽ የውሃ ሚኒስትሮች ስብሰባ በኋላ የድርድሩ ሁኔታ ሳይካሄድ ቆይቷል። አዲሱ የሱዳን መንግስት ካቢኔ በቅርቡ መቋቋምን ተከትሎ መስከረም 4 እና 5 ቀን 2012 ዓ ም በግብጽ ካይሮ የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በካይሮ የሶስትዮሽ ስብሰባ አድርገዋል። ይሁንና ግብጽ ባለፈው አንድ ዓመት ተቋርጦ የነበረው ድርድር በተለየ አካሄድ መቀጠል እንዳለበት በመግለፅ የግድቡን የውሃ ሙሌት በተመለከተ ባቀረበችው አዲስ ምክረ ሀሳብ ላይ ውይይት እንዲደረግ ሀሳብ አቅርባለች። የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ዛሬ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ግብጽ ብቻዋን ከቀድሞ ድርድር የተለየ አዲስ ንድፈ ሀሳብ ማቅረብ እንደማትችል ከኢትዮጵያ በኩል ምላሽ መሰጠቱን ገልጸዋል። ግብጽ የሶስቱም አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና የውሃ ሚኒስትሮች በጋራ እንዲወያዩ ሀሳብ ያቀረበች ሲሆን ይህም ተቀባይነት አጥቶ የውሃ ሚኒስትሮችና የቴክኒክ ኮሚቴው ብቻ እንዲወያዩ መደረጉን ነው ያብራሩት። የውይይት አጀንዳውም ቢሆን ባለፈው ዓመት የነበረው አጀንዳ መነሻ እንዲሆን ኢትዮጵያ ማሳወቋን ገልጸዋል። እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ግብጽ ያቀረበችው አዲስ ንድፈ ሀሳብ አጀንዳው ላይ መቅረብ አለበት የሚሉ ክርክርች ተነስተዋል። ይህ አጀንዳ በዚህ ውይይት ሳይሆን በሌላ መድረክ መታየት አለበት፤ "ካለፈው ዓመት ካቆምንበት ክርክር እንጀምር" የሚሉ ሀሳቦችም ተነስተዋል። በዚህ ስብሰባ ግብጽ ይዛ የቀረበችውን አዲስ ምክረ ሀሳብ ኢትዮጵያ ውድቅ ያደረገችበት ምክንያት ሀሳቡ ከውይይቱ ሂደት ያፈነገጠና በሌላ አገር ግድብ ላይ ውሳኔ የመስጠት ጉዳይ በመሆኑ ነው ብለዋል። ግብጽ ባቀረበችው አዲስ ምክረ ሀሳብ የህዳሴ ግድቡ የውሃ ሙሌት በሰባት ዓመት እንዲሆን፣ ኢትዮጵያ በዓመት 40 ቢሊየን ሜትር ኪዮብ ውሃ እንድትለቅ እንዲሁም የአስዋን ግድብ የውሃ መጠን ከምድር ወለል በላይ 165 ሜትር ላይ ሲደርስ የግድቡ ዋና ስራ ውሃ መልቀቅ ብቻ እንዲሆን የሚል ነው። ኢትዮጵያ በቀጣዩ የሶስትዮሽ ስብሰባ ግድቡ ሳይንሳዊና አሳማኝ እንዲሁም የሀገርን ጥቅም ሙሉ በሙሉ በሚያስጠብቅ መልኩ ውሃ የሚሞላበትን መንገድ ምክረ ሀሳብ ታቀርባለች ብለዋል። እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ሱዳንም የራሷን ምክረ ሀሳብ የምታቀርብ ሲሆን ኢትዮጵያ የምታቀርበው ምክረ ሀሳብ ቀደም ሲል አቅርባው ከነበረው ብዙም የተለየ አይሆንም ነው ያሉት። በሌላ በኩል እስካሁን ባለው ሂደት በግድቡ ግንባታ ላይ መጓተት ባለመኖሩ በሚቀጥለው ዓመት ታህሳስ ወር ላይ ሁለቱ ተርባይኖች ሃይል ማመንጨት እንደሚጀምሩ ሚኒስትሩ ዶክተር ስለሺ አስታውቀዋል። የሶስቱ አገሮች ብሄራዊ ገለልተኛ የሳይንስና የምርምር ኮሚቴ የህዳሴ ግድቡ እንዴትና በምን አይነት መንገድ ይሞላ፤ አሞላሉ በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ላይ በተለይም በግድቦችና ሃይል ማመንጨት ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሚካሄድበትን ሁኔታ የሚያጠና ነው።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም