ኤጀንሲው ሶስተኛ ወገን የመድን ዋስትና ባልገቡ ተሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መውሰድ ሊጀምር ነው

108
መስከረም 7/2012 የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ በመላ አገሪቷ ሶስተኛ ወገን የመድን ዋስትና ሳይገቡ እንዲሁም ውላቸውን ሳያድሱ በሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መውሰድ ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ። የኤጀንሲው የፋይናንስ ዳይሬክተር አቶ ሰፊው ምስጋናው ለኢዜአ እንደገለፁት በአሁኑ ወቅት ሶስትኛ ወገን የመድን ዋስትና አሟልተው የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ቀደም ሲል ከነበረበት 64 በመቶ ወደ 88 በመቶ አድጓል። ይህም በመሆኑ በተሽከርካሪ አደጋ ጉዳት የሚደርስባቸው ሰዎች የካሣ ክፍያ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። አሁን ላይ 12 በመቶ የሚሆኑ ተሽከርካሪዎች ሶስተኛ ወገን የመድን ዋስትና የሌላቸው መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሰፊው የሚጠበቅባቸውን አሟልተው እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ ጥብቅ ቁጥጥር ይጀመራል ብለዋል። በኤጀንሲው የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኮማንደር ተሾመ ፈየራ እንዳሉት፤ ከዛሬ ጀምሮ ያለ3ኛ ወገን የመድን መለያ ሲንቀሳቀስ የተገኘ ባለሞተር ተሽከርካሪ ባለቤት በህጉ መሰረት ከ1 እስከ 2 ዓመት እስራት ወይም ከ3 ሺህ እስከ 5 ሺህ ብር ቅጣት ይጠብቀዋል። ለዚህም በክልሉ ከዛሬ ጀምሮ ጥብቅ ቁጥጥር በማድርግ እርምጃ መውስድ ይጀመራል ብለዋል። አዲስ ለሚገቡና የውል ዕድሳት ጊዜ ላለፈባቸው ተሽከርካሪዎች አገልግሎት የሚሰጡ 17 የመድን ተቋማት በኤጀንሲው ዕውቅና ቢሮ ከፍተው አገልግሎት እንዲሰጡ መመቻቸቱንም ገልጸዋል። የመድን ህጉ ማንኛውንም የሞተር ተሽከርካሪ የመድን ዋስትና ሳይኖረው በመንገድ መንቀሳቀስን፣ ለሌላ አካል አሳልፎ መስጠትን ይከለክላል። ከወራት በፊት ሁሉም ተሽከርካሪዎች የሶስተኛ ወገን የመድን ዋስትና አሟልተው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ሲነገር ቆይቷል ተብሏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም