በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ዝግጅት ተደርጓል

56
መስከረም 7/2012  በዲላ ዩኒቨርሲቲ የነበረው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት በተያዘው የትምህርት ዘመንም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ዝግጅት መደረጉ ተገለፀ፡፡ ዩኒቨርሲቲው በተማሪዎች አገልግሎት ዙሪያ ቅሬታ ሊነሳባቸው ይችላሉ ያላቸውን ጉዳዮች በመለየት የማስተካከያ እርምጃ መውሰዱንም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ተናግረዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ዶክተር ችሮታው አየለ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፈው አመት ዩኒቨርሲቲው ከተማሪዎችና ከአከባቢው ማህበረሰብ ጋር ተቀራርቦ በመስራቱ የመማር ማስተማር ሂደቱ በሰላም ተጠናቋል፡፡ በተያዘው የትምህርት ዘመንም የተገኘውን ሰላም አጠናክሮ ለማሰቀጠል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከሀገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች እንዲሁም ከዲላ ከተማና ከጌዴኦ ዞን አስተዳደር የተወጣጣ ኮሚቴ በማዋቅር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በተማሪዎች አገልግሎት ዙሪያ ቅሬታ ሊነሳባቸው የሚችሉ ጉዳዮችን በመለየትም የማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ በተለይ በዩኒቨርሲቲው ላለፉት አምስት አመታት ጥያቄ የነበረው የውሃ ችግር የተጀመሩ የውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮ ፕሮጀክቶች በመጠናቀቃቸው ችግሩ ሙሉ ለሙሉ መቀረፉን ጠቅሰዋል፡፡ የተማሪዎች ማደሪያ እድሳት የተደረገላቸው ሲሆን የምግብ አገልግሎትን ለማስተካከልም በቂ ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ አክለውም በተያዘው የትምህርት ዘመን የትምህርት ስርዓቱ መቀየሩን ተከትሎ በተወሰኑ የትምህርት ክፍሎች ላይ ጫና እንዳያሳደር የመምህራን ቅጥር እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ነባርና አዲስ ገቢ ተማሪዎቹን በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ውስጥ የሚቀበል ሲሆን ግቢ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል እንደሚጠብቃቸውም ተናግረዋል፡፡ የዝግጀት ኮሚቴ አባል የሆኑት የዲላ ከተማ ከንቲባ አቶ ትግሉ በቀለ በበኩላቸው ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው ሲመጡ ደማቅ አቀባበል ለማድረግ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸው፡፡ በቆይታቸውም ትምህርታቸውን በሰለምና በተረጋጋ መንፈስ እንዲከታተሉ የከተማ አስተዳደሩ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የከተማው ነዋሪዎችም እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደራሱ ልጆች ለመከባከብ ከስምምነት መድረሱን አስታውቀዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ዘንድሮ የሚቀበላቸውን ከ3 ሺህ 600 በላይ አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ጨምሮ በተለያዩ መረሃ ግብሮች ከመጀመሪያ እስከ ሶስተኛ ድግሪ ከ31 ሺህ 200 በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ከዩኒቨርሲቲው የተገኘ መረጀ ያስረዳል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም