በባህር ዳር ከተማ 497 ሽጉጥና ከ37 ሺህ 700 በላይ ጥይት ተያዘ

65
በባህር ዳር ከተማ በነዳጅ ቦቴ ውስጥ ተደብቆ ሲዘዋወር የነበረ 497 ሽጉጥ ከ37 ሺህ 700 በላይ ጥይት ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአማራ ክልል አድማ ብተና ፖሊስ አስታወቀ። የክልሉ አድማ ብተና ፖሊስ የሻምበል ሃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ታለማ ዳኘ ለኢዜአ እንደገለፁት ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያው የተያዘው ከመተማ ጀምሮ በተደረገ ጥብቅና ሚስጥራዊ ክትትል አማካኝነት ነው። ከህብረተሰቡ የደረሰ ጥቆማን መሰረት በማድረግ በተደረገው ክትትልም ትናንት ማታ ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት እስከ 4፡00 ሰዓት ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በባህርዳር ከተማ በአንድ ነዳጅ ማደያ ውስጥ ሊያራግፍ ሲል መያዙን ተናግረዋል። ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያው በቦቴው ውስጥ በማዳበሪያ ተጠቅልሎ የተገኘ መሆኑን የገለጹት ምክይል ኢንስፔክተር ታለማ ከብሄራዊ ደህንናት ጋር በመቀናጀት በተደረገው ክትትልም ለማምለጥ ሙከራ ያደረገውን አሽከርካሪም በቁጥጥር ስር ማዋል እንደተቻለ አስረድተዋል። መሳሪያውን ያስመጣው አካል እስከ አሁን አለመያዙን ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ የህገ-ወጥ እንቅስቃሴን  በመታገል ለጸጥታ ሃይሉ የሚሰጠው ጥቆማ ጠንካራ መሆኑንም አብራርተዋል። በቀጣይም መሰል ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን ሲመለከት በአካባቢው ለሚገኝ የፀጥታ መዋቅር በመጠቆም የተረጋጋ ሰላምና ደህንነት እንዲፈጠር የሚያደርገውን እገዛ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም